"በንፁሃን ላይ የተጣለ የፈሪዎች ጥቃት" ብለውታል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሣ ሜይ ትናንት ማታ ማንቸስተር ላይ የደረሰውን የሃያ ሁለት ሰው ሕይወት የቀጠፈውን አደጋ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከእንግሊዝ ሕዝብ ጎን በፅናት እንደምትቆም ፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትረምፕ አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ ታዳጊ ወጣቶች ዘንድ ተፈቃሪ የሆነችው አሜሪካዊት ኮከብ ዘፋኝ አሪያና ግራንዴ እንግሊዟ ከተማ ማንቸስተር ላይ የሙዚቃ ትርዒቷን እንዳጠናቀቀች ነበር 21 ሺህ ወጣት ተመልካቾችና ወላጆቻቸው በታጨቁበት ግዙፍ ቴአትር ደጃፍ ላይ አስደንጋጩ ፍንዳታ የደረሰው፡፡ በአደጋው ሃያ ሁለት ሰው መሞቱ ተረጋግጧል፤ 59 ሰዎች ቆስለዋል፡፡
በኮንሰርቱ ላይ የነበሩ አብዛኞቻቸው ልጃገረዶች የሆኑ በሺሆች የሚቆጠሩ በፍንዳታውና በተፈፀመው ጥቃት እጅግ የተደናገጡ ታዳሚዎች ከአካባቢው ለመሸሽ ሲተራመሱ ታይተዋል፡፡ በኮንሰርቱ ከነበሩ ተመልካቾች አንዷ ሶፊ ዋከር ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበረ ስትገልፅ እንዲህ ብላለች፡- "ኮንሰርቱ እንዳለቀ መብራት በራ፤ ሰዉም ከየተቀመጠበት ተነሣ፡፡ ወዲያው እጅግ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማ፡፡ መቀመጫዎቹ ሁሉ ተናጡ፤ ሁሉም ሰው መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ብዙ ጩኸትና ለቅሶ ነበረ፡፡ ሁላችንም በአቅራቢያችን ያለ መውጫ ነበር የምንፈልገው፡፡ እኛ ከኋላ የነበረ የላይኛው አካባቢ ስለነበርን መሹለኪያ ለማግኘት ዙሪያውን መሄድ ነበረብን፡፡"
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ