ዋሽንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል የኮቪድ-19 ክትባትን አንወስድም ያሉ 27 ሰዎችን ከሠራዊቱ ማባረሩን አስታወቀ፡፡
አሶሼትይድ ፕሬስ እንደዘገበው የአየር ኃይሉ የክፍሉ ባልደረቦች እኤአ እስከ ህዳር 2 ድረስ የኮቪድ-19 ክትባትን እንዲወስዱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ ወይም በተለያየ ምክንያ ከክትባቱ ነጻ እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር አባላት መኖራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአየር ኃይሉ ቃል አቀባይ አን ስቴፋኔክ ትንናት በሰጡት መግለጫ ክትባቱን አስመልክቶ ይህ የመጀመሪያው ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው እንዲባረሩ የተደረጉት አዲስ ተቀጣሪዎች ወጣቶችና በዝቅተኛ የማዕረግ ደረጃ የሚገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ትዕዛዝ ሁሉም የሠራዊቱ አባላት እንዲከተቡ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ትዕዛዙን በማያከብሩት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
ዛሬ 96 ከመቶ የሚሆኑን የሠራዊቱ አባላት ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት መውሰዳቸውም ተመልክቷል፡፡