በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና ጁባላንድ መካከል ውጊያ ተቀሰቀሰ


ጁባላንድ፣ ሶማሊያ
ጁባላንድ፣ ሶማሊያ

በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና በጁባላንድ የክልል አስተዳደር መካከል ለሳምንታት የቆየው የፖለቲካ ልዩነት እና ውጥረት ተባብሶ፣ በደቡብ ሶማሊያ ግጭት ተቀስቅሷል።

ግጭቱ የተካሄደው፣ በቅርቡ የፌደራል ኃይሎች በተሰማሩባት ራስካምቦኒ የተሰኘች ከተማ ነው። ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በመቀስቀር እርስ በእርስ የተወነጃጀሉ ሲሆን፣ ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን በውል አልታወቀም።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ውዝግቡ የተቀሰቀሰው በቅርቡ በጁባላንድ የተደረገውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ሲሆን የፌደራል መንግስቱ ሕገወጥ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል።

በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና ጁባላንድ መካከል ውጊያ ተቀሰቀሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:59 0:00

በፌደራሉ አመራር እና በክልሉ አስተዳደሪዎች መካከል እየተካረረ የሄደው የፖለቲካ ውዝግብ ተባብሶ፣ ረቡዕ እለት በፌደራል መንግስቱ ወታደሮች እና በጁባላንድ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ መካሄዱ ተገልጿል።

በአካባቢው የስልክ መስመር በመቋረጡ ዝርዝር መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ በጁባላንድ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች የመጀመሪያውን ጥቃት የፈፀሙት የፌደራል ኃይሎች ናቸው በማለት ይከሳሉ። የጁባላንድ ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ኤደን አህመድ ሃጂ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ከሞቃዲሾ ወደ ራስካምቦኒ የመጡት የፌደራል ኃይሎች በጁባላንድ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል። ጥቃቱ የጀመረው በድሮን ሲሆን፣ ውጊያው እየተካሄደ ያለው ከከተማ ወጣ ብሎ ነው። ግጭቱ ተስፋፍቶ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የመንግሥት ኃይሎች አንድ ክፍል እጁን ሰጥቷል" ብለዋል።

ጁባላንድ በርካታ የፌደራል መንግስት ወታደሮች እጃቸውን መስጠታቸውን የምትገልፅ ሲሆን፣ የክልሉ ባለስልጣናትም የፌደራል ኃይሎች የሚጠቀሟቸውን ሰው አልባ አሮፕላኖች የሰጡ ሀገራትን ስም ዝርዝር ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።

"የሁለቱም ወገኖች ወታደሮች በአንድ መከላከያ ኃይል ውስጥ የሚገኙ ወንድማማቾች ሆነው ሳለ፣ ዛሬ እርስ በእርስ መተኳኮሳቸው በጣም ያሳዝናል" ያሉት የጁባላንድ የደህንነት ሚኒስትር፣ "የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ኃላፊነት ነው። የሶማሊያን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያገለግሉ ጦር መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪዎች በሕዝብ ላይ ለጥቅም መዋላቸው የሚያሳዝን ነገር ነው" ሲሉ ፌደራል መንግስቱን ወንጅለዋል።

የሶማሊያ ፌደራል መንግስት መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ "ያልተጠበቀ ጥቃት" ሲል የገለፀውን ጥቃት፣ በፌደራል ወታደሮች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ስፍራ እና ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚሰጡ የአካባቢው ሰራተኞች ላይ በማድረስ የጁባላንድ ኃይሎችን ከሷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫም የፌደራል ኃይሎች በአካባቢው የሰፈሩት፣ የአፍሪካ ህብረት ኃይሎች በቅርቡ የለቀቁትን ወታደራዊ ካምፕ ለመረከብ እና በአልሻባብ ላይ የጸረ ሽብር ዘመቻዎች ለማዘጋጀት መሆኑን ገልጿል።

ሆኖም ሁለቱም ወገኖች የሚያቀቧቸውን ክሶችም ሆነ ውጊያው በምን ያክል መጠን እየተካሄደ መሆኑን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም።

የሶማሊያ መንግስት በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ራስካምቦኒ ከተማ ውስጥ ያሰፈረ ሲሆን፣ ጁባላንድ ድርጊቱ የክልሉን ደህንነት እና አስተዳደር ለማዳከም የተደረገ ነው ብሏል። የፌደራል ባለስልጣናቱ ግን፣ ወታደሮቹ የሰፈሩት ከአፍሪካ ህብረት መውጣት ጋር ተያይዞ በቦታው የነበሩት የኬንያ ኃይሎች ስፍራውን በመልቀቃቸው ነው ሲል ይከራከራል።

ጁባላንድ በራስካምቦኒ ከተማ የስልክ አገልግሎቶችን ያቋረጠ ሲሆን፣ የፀጥታ አካላትንም በአካባቢው አሰማርቷል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድን "ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም" የምትከሰው እና የፌደራል መንግስቱ ሕገመንግስቱን ጥሷል የምትለው ጁባላን ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ሕዳር 19፣ 2017 ዓ.ም አስታውቃለች። ፓርላማው ያሳለፈውን ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ እንደማትቀበልም ገልጻለች።

አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሞቃዲሾ የሚገኝ ፍርድ ቤት፣ "አህመድ ማዶቤ" በሚል ስያሜ የሚታወቁትን የጁባላንድ መሪ አህመድ ሞሃመድ ኢስላም፣ በሀገር ክህደት እና የሀገር ሚስጥርን ለውጭ ሀገር በማጋራት ሕገመንግስትን የሚፃረር ድርጊት ፈፅመዋል በማለት የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸዋል።

ውዝግቡ የተቀሰቀሰው አህመድ ማዶቤ በጥቅምት ወር በሞቃዲሾ ከተካሄደው ብሔራዊ የምክክር ምክርቤት ስብሰባ አቋርጠው ከወጡ እና በሕዳር ወር ምርጫ በማካሄድ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ከተመረጡ በኃላ ነው።

ክልሉ ቀጥተኛ ምርጫ ማካሄዱን የተቃወመው የፌደራል መንግስት ሂደቱን ውድቅ አድጓል። በወቅቱ የፌደራል መንግስት እና አንዳንድ የክልል አመራሮች የአካባቢ ምርጫዎችን በሰኔ ወር፣ የክልል ፓርላማ እና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎችን ደግሞ በመስከረም 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ተስማምተው ነበር። ጁባላንድ ግን ይህን ስምምነት አልተቀበለችውም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG