በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ፓርላማ በአል-ሻባብ ጥቃት ተመታ፤ ጅቡቲ ውስጥ ፍንዳታ ደረሰ


በሶማሊያ ፓርላማ ላይ ጥቃት እንደተፈፀመ የተኩስ ምላሽ እየሰጠ የነበረ የሶማሊያ ወታደር - ግንቦት 16/2006 ዓ.ም - ሞቃዲሾ/
በሶማሊያ ፓርላማ ላይ ጥቃት እንደተፈፀመ የተኩስ ምላሽ እየሰጠ የነበረ የሶማሊያ ወታደር - ግንቦት 16/2006 ዓ.ም - ሞቃዲሾ/

የሶማሊያ የፀጥታ ሚኒስትር ሥራቸውን ለቀቁ






የአል-ቃይዳ ግብር አበር የሆነው አል-ሻባብ በሶማሊያ ፓርላማ ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ 18 ሰው መገደሉ ተገልጿል፡፡

አል-ሻባብ ጥቃቱን ያደረሰው በፓርላማው ላይ ከፈፀመው ድንገተኛ ወረራ ጋር በቦምብ የታጨቁ መኪኖችንና አጥፍቶ ጠፊ ታጣቂዎቹን አሠራማረቶ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የሶማሊያ መንግሥትና የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ - አሚሶም አባላት የሁኑ አሥር የፀጥታ ጥበቃ ባልደረቦች መገደላቸውን የሃገሪቱ ፖሊስ ቃልአቀባይ ቃሲም አህመድ ሮብሌ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ከባድ ጥበቃ በሚደረግለት ፓርላማ ላይ በተጣለው በዚህ አደጋ ከተገደሉት 18 ሌላ 14 ሰዎች መቁሰላቸውና ከቆሰሉት መካከል አራት እንደራሴዎች እንደሚገኙ ሮብሌ አክለው ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲልም ፓርላማው የጥቃት ዒላማ ሊሆን እንደሚችል እና የፀጥታ ጥበቃው መጠናከር እንዳለበት የሚያሳስብ ጥያቄ ከሃገር ውስጥ ፀጥታ ኮሚቴ ቀርቦ እንደነበር የፓርላማው የመከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሁሴን አራብ ኢሴ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

ያ ጥቆማና ጥያቄ የሚገባው ትኩረት እንዳልተሰጠውና ችላ እንደተባለ እንደራሴ ኢሴ አክለው አመልክተዋል፡፡

የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲዌሊ ሼህ አህመድ ጥቃቱን አውግዘው “ሽብር ፈጣሪዎች የሁሉም ሶማሌዎች ፀር መሆናቸውን በድጋሚ አሳዩ” ብለዋል፡፡

“የፍርሃትና ሊገል የማይችል አድራጎታቸው የእውነተኛ እስላማዊነት መገለጫ አይደለም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲዌሊ አክለው፡፡
የሶማሊያ ጦር እና የአሚሶም የፀጥታ ክፍሎች ሰጥተዋል ያሉትን ፈጣን ምላሽም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙንም “ጥቃቱን ማውገዛቸውንና ለእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት አንዳችም አሣማኝ ሊሆን የሚችል ሰበብ የለም” ማለታቸውን ፅ/ቤታቸው አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ይህንን በሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፓርላማ ላይ የተፈፀመ ጥቃት በቁጣ አውግዟል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ምላሹ ፈጣን ነበር ሲሉ አድንቀው ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች፣ ለሶማሊያ መንግሥትና ለአሚሶም ኀዘኑን ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ይህ አል-ሻባብ እኔ ነኝ ያደረስኩት ያለው ጥቃት ከተፈፀመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የሶማሊያ ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር አብዲካሪም ሃሰን ጉሌድ ሥራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኽ ሞሐመድ የቅርብ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት ጉሌድ ሥራቸውን የለቀቁት እንዲለቅቁ ተጠይቀው ይሁን ወይም በራሣቸው ተነሣሽነት ለጊዜው የወጣ መረጃ የለም፡፡

ፕሬዚዳንቱ የሚገኙት ለጉብኝት በተጓዙባት ደቡብ አፍሪካ መሆኑም ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ የውጭ ዜጎች ያዘወትሩታል በሚባል ጅቡቲ ከተማ ውስጥ ሁለት የእጅ ቦምቦች ተጥለው ሁለት ሰዎች መገደላቸውን “ሎ ሞንድ” የሚባለውን የፈረንሣይ ጋዜጣ ጠቅሶ የቪኦኤ የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍል ዘግቧል፡፡

“የወንጀል አድራጎት ነው፤ ሁለት ተገድለው አሥራ አንድ ቆስለዋል” ብለዋል የጅቡቲ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ፡፡

የጅቡቲውን ጥቃት ያደረሰው ማን እንደሆነ አልተገለፀም ከዛሬው የሞቃዲሾ አደጋ ጋርም ግንኙነት ይኑረው ወይም አይኑረው አይታወቅም፡፡
XS
SM
MD
LG