በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለሶማሊያው ጦር ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጡ


የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለሶማሊያው ጦር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለሶማሊያው ጦር

ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ያሏትን ወታደሮቿን በማውጣት ኃላፊነቷን አታሣንስም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ፡፡




የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ
የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ

please wait

No media source currently available

0:00 0:05:06 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ያሏትን ወታደሮቿን በማውጣት ኃላፊነቷን አታሣንስም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የሃገራቸውን አቋም ያሳወቁት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ሰሞኑን ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር ሶማሊያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጦር በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀው እንደነበረ ይታወሣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የመንግሥታቸውን የስምንት ወር የሥራ አፈፅፀም ሪፖርት ባቀረቡበት የፓርላማው ማብራሪያቸው ወቅት የሠራዊታቸውን ከሶማሊያ መመለስ ለማፋጠን እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ
የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ነው ያሉትን አልሻባብን ከመታገልና ከማክሰም ወደኋላ እንደማይሉ ለሶማሊያ ሕዝብና መንግሥትም ማሳወቃቸውን ገልፀው አሁን ባለው ሁኔታ ጦሩን እንደማያስወጡና ከውጊያውም እንደማያፈግፍጉ አመልክተው ነበር፡፡

ከጥቂት ሣምንታት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ሁዱር ከምትባለው ስትራተጂክ ከተማ ድንገት መውጣታቸው በአካባቢው የፀጥታ ክፍተት መፍጠሩና የአልሻባብ ተዋጊዎችም ወዲያው የኢትዮጵያን እግር መውጣት ተከትለው ከተማይቱን መቆጣጠራቸው ይታወቃል፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ በነሐሴ 2003 ዓ.ም ዋና ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ ለቅቀው እንዱወጡ ለተገደዱት ፅንፈኛ ናቸው ለሚባሉት ቡድኖች የተወሰነ የመሬት ድል እንዳስጨበጣቸውም ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሁዱርን ለቅቆ መውጣት የአፍሪካ ኅብረቱና የመንግሥታቱ ድርጅት ጦር - አሚሶም አክራሪዎቹን ጠራርጎ ለመምታት እየተንቀሣቀሰ ነው በሚባልበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከአልሻባብ ጋር ከገጠመችው ውጊያ “እያፈገፈገች ለመሆኗ ፍንጭ ይሰጣል” የሚሉ ግምቶችንና ንግግሮችን በስፋት አስነስቶ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ትናንት - ሐሙስ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ጦር ከሁዱር እንደሚወጣና ቀጥሎም ከክልሉ ዋና ከተማ ከባይዶዋ እንደሚነቅል ቀደም ሲል ተነግሮ ገልፀዋል፡፡

“ይህ ጉዳይ የተዛባ መረዳትን ያዘለ በመሆኑ ማብራሪያ ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ስለመውጣቷ ማንንም አላማከረችም ወይም የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አልሰጠችም የሚለው ጥያቄ መሠረተ-ቢስ ነው፡፡ ሊያውቁ የሚገባቸው ከመውጣታችን በብዙ ወራት በፊት እንዲያውቁ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያለመግባባት የለም፡፡ የተፈጠረው ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ ኃላፊነትና ድርሻ በምንም አያሣንሰውም፡፡” ብለዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ በመንግሥታቸው በኩል ያለውን በየጊዜው እያደገ የመጣ ቅሬታም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጎረቤቷን የሶማሊያን ደኅንነት ለመከላከል የምታወጣውን ግዙፍ ወጭ ያለአንዳች የገንዘብ እርዳታ እራሷ እየሸፈነች መቀጠሏና በበቂ በጀት የሚንቀሣቀሰው አሚሶም የኢትዮጵያን ወታደሮች ይተካል የተባለውም ቃል ሳይጠበቅ መቅረቱ አዲስ አበባን እያሳሰባትና እያበሣጫት ይገኛል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ በዚሁ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ማብራሪያቸው “ወጭን የመካፈል ጥያቄ ለእኛ ሁልጊዜ የሥጋታችን ምንጭ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠው ጥያቄ ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር የተሠማራው ሶማሊያ ውስጥ እየታየ ያለውን ግስጋሴ ሊያደናቅፍ የሚችለውን ሥጋት ለመጋፈጥ ተጨማሪ እሴት ሊኖረው በሚችል ሁኔታ ነው ወይ የሚል ነው፡፡ የእኛ ድምዳሜ አይደለም፤ የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ሶማሊያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት በምንም አይቀንሰውም፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል እንዳልኩት ወጭን ለመካፈልና አሁን ግዳጅ ላይ ያሉትን ኃይሎች በአግባቡ የመጠቀምን አስፈላጊነት ለሚመለከቱት ጉዳዮች ነው አሁን ቀዳሚውን ወይም ግዙፉን ቦታ የምንሰጠው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ልንገነጋገርባቸው የምንፈልጋቸውም ጉዳዮች እነዚሁ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በዚህ ሣምንቱ የፓርላማው ንግግራቸው ሠራዊቱን ከሶማሊያ እንደሚያስወጡ አልተናገሩም፡፡ ይሁን እንጂ የአሚሶም ኃይሎች “ከዛሬ ነገ መጥተን እንረከባለን እያሉ” የኢትዮጵያ ወታደሮች ባሉበት እንዳሉ አንድ ዓመት ማለፉን በመጥቀስ ወቅሰዋል፡፡

ይህ አባባላቸውም ከሁዱር የወጡት “አንዳች ትኩረት ለማግኘት ሲሉ ነው” የሚል ግምትም በታዛቢዎች ዘንድ እንዲያድር ማድረጉ እየተሰማ ነው፡፡

አብዛኛው ሠራዊት የተውጣጣው ከዩጋንዳ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኬንያ፣ ከሲየራ ሌዖንና ከጅቡቲ የሆነው የአሚሶም ጦር ከአውሮፓ ኅብረትና ከአፍሪካ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል፡፡

የኢትየጵያ ጦር የአሚሶም አካል ባለመሆኑ ምክንያት ሙሉው ወጭው የሚሸፈነው በራሷ በኢትዮጵያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
XS
SM
MD
LG