በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፓሪሱ ጥቃት “የጦርነት አድራጎት” እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናገሩ


ከሽብር ጥቃቶቹ በኋላ - ፓሪስ
ከሽብር ጥቃቶቹ በኋላ - ፓሪስ

ከ120 በላይ ሰው የተገደለበትን የትናንቱን የፓሪስ ጥቃት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ “የጦርነት አድራጎት ነው ሲሉ ጠርተውታል፡፡

ጥቃቶቹ ከተፈፀሙባቸው ስድስት የዋና ከተማይቱ ሥፍራዎች አንደኛው ከሆነው የባታክላን የሙዚቃ ዝግጅት አዳራሽ ፊትለፊት ባለው አደባባይ ላይ ዛሬ ኀዘንተኞች ተሰብስበው ነበር
ጥቃቶቹ ከተፈፀሙባቸው ስድስት የዋና ከተማይቱ ሥፍራዎች አንደኛው ከሆነው የባታክላን የሙዚቃ ዝግጅት አዳራሽ ፊትለፊት ባለው አደባባይ ላይ ዛሬ ኀዘንተኞች ተሰብስበው ነበር

የፓሪሱ ጥቃት “የጦርነት አድራጎት” እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:57 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የፓሪሱ ጥቃት “የጦርነት አድራጎት” እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናገሩ

ከ120 በላይ ሰው የተገደለበትን የትናንቱን የፓሪስ ጥቃት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ “የጦርነት አድራጎት ነው ሲሉ ጠርተውታል፡፡

ለጥቃቱ ‘እሥላማዊ መንግሥት ነኝ’ የሚለው ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ተኩስ ከፍተው ብዙ ከፈጁበትና ብዙ ሰውም በታጋችነት ይዘው ከነበረበት ጥቃቶቹ ከተፈፀሙባቸው ስድስት የዋና ከተማይቱ ሥፍራዎች አንደኛው ከሆነው የባታክላን የሙዚቃ ዝግጅት አዳራሽ እስከዛሬ ማለዳ አስከሬኖች እየወጡ ነበር፡፡

ፖሊስ ወደ አዳራሹ ሰብሮ ከገባ በኋላ ከጥቃት አድራሾቹ አንዱን ሲገድል ሌሎቹ ግን እራሣቸውን አፈንድተው ከሰዉ ጋር አጥፍተዋል፡፡

የፓሪስ የሽብር ጥቃቶች
የፓሪስ የሽብር ጥቃቶች

ፕሬዚዳንቱ በመላ ሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ያወጁ ሲሆን ሌሎችም ጥቃቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ በሚል ሥጋት ባለሥልጣናቱ በመላ ፈረንሣይ ፀጥታ አስከባሪዎችን አሠማርተዋል፡፡

በፓሪስ ላይ በተፈፀሙት ተደራራቢ ጥቃቶች ኀዘናውንና ንዴታቸውን የገለፁ የዓለም መሪዎች ከፈረንሣይ መንግሥትና ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ እያሣወቁ ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባስተላለፉት መልዕክትም ተመሣሣይ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስለፈረንሣይ የሽብር ጥቃት ሲናገሩ /ዋይት ሃውስ፣ ኅዳር 3/2008 ዓ.ም/
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስለፈረንሣይ የሽብር ጥቃት ሲናገሩ /ዋይት ሃውስ፣ ኅዳር 3/2008 ዓ.ም/

“ፈረንሣይ የጥንት ወዳጃችን ነች፡፡ የፈረንሣይ ሕዝብ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በተደጋጋሚ ትከሻ ለትከሻ ቆሟል፡፡ እኛም እነርሱ ከሽብርተኝነትና ከፅንፈኝነት ጋር እያደረጉ ባሉት ጦርነት ከጎናቸው እንቆማለን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ኦባማ፡፡

አሜሪካ ፈረንሣይ የምትፈልገውን ማንኛውንም እገዛ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗንም ፕሬዚዳንት ኦባማ ገልፀዋል፡፡

ለፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት እየደወሉም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ባደረጓቸው ንግግሮች ኀዘናቸውንና ቁጣቸውን ከገለፁት መሪዎች መካከል የቫቲካን ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ “ይህ አድራጎት በማንኛውም ሃይማኖትም ይሁን በሰው ዘንድ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፡፡

የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል “ይህ ጥቃት በነፃነት ላይ የተፈፀመው በፓሪስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁላችንም ላይ ነው፤ ሁላችንንም ይጎዳናል፡፡ ለዚህም ነው መልሱን ሁላችንም አብረን የምንሰጠው” ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን የእሥላማዊ መንግሥት ቡድንን ታጣቂዎች “ጨካኝና ርኅራሄ የለሽ ነፍሰ ገዳዮች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡ ሃገራቸው “መርዛማ ፅንፈኛ” ያሉትን አስተሳሰብ ለማጥፋት ጥረቷን እንደምታጠናክር ዝተዋል፡፡

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “የውንብድና አድራጎት” ብለውታል፡፡

በኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮውሃኒ በአውሮፓ ሊያደርጉት አቅደውት የነበረውን የአራት ቀናት ጉብኝት ሠርዘው ጥቃቶቹን “በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች” ብለዋቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን “አሣፋሪ የሽብር ጥቃቶች” ብለዋቸዋል፡፡

የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ ለፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በፃፉት ደብዳቤ “ፓሪስ ላይ የተፈፀመው አሣዛኝና ወራዳ የሽብር አድራጎት ሊከፋፍለን፣ ሊያስደነብረንና ፈረንሣይን ታላቅ መንግሥት የሚያደርጓትን እሴቶች ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን ሊጠፋ እንደማይችል፤ በዚህም ዒላማውን እንደማይመታ እናረጋግጣለን” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጃን ኬሪና ሰርጌይ ላቭሮቭም በሶሪያ ጉዳይ ከተቀመጡበት የኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና ጉባዔያቸው አውግዘውታል፡፡

የትናንትናውንና በቅርቡም የተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶችን “… በአንድ ጊዜ የመካከለኛው ዘመንና ዘመናዊውን ፋሺዝም የሚመስሉ፤ ለሰው ልጅ ሕይወት አንዳች ክብር የሌላቸው፣ ለውድመት የሚካሄዱ፣ ቀውስን፣ ሥርዓት ዐልበኝነትና ፍርሃትን ለማንገሥ የሚፈልጉ…” እንደሆኑ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ለቡድን ሃያ ስብሰባ ወደ ቱርክ ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞ ሠርዘዋል፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ

“ሽብርተኞች እንዲህ ዓይነቶቹን የጭካኔ አድራጎቶች ሲፈፅሙ፣ ከፊታቸው ተደቅና የሚያገኟት በቁርጠኝነቷ የፀናች ፈረንሣይን፣ አንድ ፈረንሣይን፣ የተሰበሰበች ፈረንሣይንና እራሷን ለመሸማቀቅ ያላሣደረች ፈረንሣይን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል” ብለዋል ሚስተር ኦሎንድ፡፡

XS
SM
MD
LG