በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአዲስ አበባ መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ


ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ካለፈው ኀሙስ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ የአንዳንድ የአዲስ አበባ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ዛሬም ማስተማር አልጀመሩም።

ለአንድ መቶ አምስት መምህራን አንድ መቶ አምስት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችን የለጠፈው የኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት አድማ የመቱት መምህራን ዛሬ ሥራ ካልጀመሩ እንደሚባረሩና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቋል።

በተፈጠረው ሕገ ወጥ ተግባር በሀገር፣ በሕዝብና በተቋም ላይ የሚደርሰው ሰብዓዊና ቁሣዊ ሃብት ውድመት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ያስጠነቅቃል።

መምህራኑ ዛሬ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የጠየቀው ደብዳቤ ይህ ካልሆነ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ ተቆጥሮ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ያሳስባል።

የሌሎች ትምህርት ቤቶች መምህራንም ተመሳሳይ የሥራ ማቆም አድማ መትተዋል።

የከፍተኛ አሥራ ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የደራርቱ ቱሉ መሰናዶ ትምህርት ቤት፣ አዲስ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እንደ ኮከበ ፅባህ ሁሉ ሥራ ያለመጀመራቸውን ምንጮች ገልፀዋል።

ለከፍተኛ አሥራ ሁለትና አዲስ ብርሃን መምህራን ተመሣሣይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷል።

በየካቲት አሥራ ሁለት ወይም በቀድሞ አጠራሩ በመነን ሁለተኛኛ መሰናዶ ትምህርት ቤትም ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ትምህርት ተስተጓጉሏል።

የመምህራኑ የተቃውሞ መነሻ ተደረገ የተባለውን የደመወዝ ጭማሪ አስመልክቶ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሰሞኑን በቴሌቪዢን የተሰጠ መግለጫ ነው።

ጭማሪውን ይፋ ያደረጉት ባለሥልጣናት የተጠቀሙበት አገላለፅ በራሱ ለተቃውሞው ምክንያት አስተዋጽዖ ማድረጉን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የጠየቁ መምህር ለቪኦኤ ገልፀዋል።

“የመምህሩን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ የሚለውጥ፣ ኑሮን የሚያሻሽል የመምህራንን ፍልሰት የሚያስቆም የቀደመውን የሙያውን ማዕረግ የሚመልስ” በማለት ክበው የተናገሩት ከደሞዝ ጭማሪው መጠን ጋር የማይጣጣምና ይልቁንም በመጋነኑ ምክንያት በመምህሩ ላይ በኪራይ ቤት ጭማሪና በመሳሰሉት ችግር የፈጠረ ነው ብለዋል።

መፍትሔ የሚሆነውም መንግሥት የጭማሪውን መጠን በግልፅ ተናግሮ መምህሩን ይቅርታ መጠየቅ ነው ብለዋል።

ዝርዝሩን ከእስክንድር ፍሬው ዘገባ ያድምጡ።

XS
SM
MD
LG