በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሳን በርናርዲኖ ግድያና የጦር መሳርያ ቁጥጥር በአሜሪካ እያከራከረ ነው


ከትናንት በስቲያ ሮብ ማታ በምዕራባዊቷ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍለ-ሀገር ካሊፎርኒያ ውስጥ በምትገኘው (San Bernardino) አውራጃ በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ 14 ሰዎች ትናንት ሐሙስ ማታ የጸሎትና የሻማ ማብራት ሥነ-ሥራት መካሄዱ ተገለጸ።

የሳን በርናርዲኖ (San Bernardino) አውራጃ፣ ከ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) ከተማ በስተምሥራቅ 100 k.m ላይ ትገኛለች። በዚህ፣ በአውራጃው የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ቢሮ ሕንፃ ላይ በደረሰው አደጋ ሌሎች 21 ሰዎች መቁሰላቸውም ይታወሳል።

ባለሥልጣናት በገለጹት መሠረት፣ ነፍሰ-ገዳዮቹ ሳይድ ሪዝዋን ፋሩክ (Sayed Rizwan Farook) እና ባለቤቱ ታሽፊን ማሊክ (Tashfeen Malik) ይህን አሰቃቂ አደጋ ያደረሱበት ምክንያት እስካሁን ለማንም ግልጽ አይደለም።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት፣ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያመት ባል ድግስ ማለት እንደ ፓርቲ ነበርና፣ እዚያ የተገኘው ፋሩቅ፣ ከአንድ የሥራ ባልደረባው ጋር ትንሽ ንትርክ ቢጤ አድርጎ ሲያበቃ ከፓርቲው ወጥቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ብዙም አልቆየ፣ ልዩ ልዩ ጦር መሣሪያዎችንና የእጅ ቦምብ ይዘው፣ የጦር ትጥቅ አድርገው ከባለቤቱ ጋር ድግሱ ወደሚካሄድበት አዳራሽ ይመለሳሉ።

ከዚያ የሆነው ግልጽ ነው-የተኩስ እሩምታ፣ ጩኸትና እሪታ፣ ሰው በሰው ላይ፣ አስከሬን ባስከሬን ላይ ተነባበረ። 75 ጥይቶች አዳራሹ ውስጥ ተርከፈከፉ፣ አሥራ-አራቱን ገደሉ፣ ሃያ-አንዱን አቆሰሉ። ከሟቾች መካከል፣ የ60 ዓመቱ የአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪ የነበሩት ኤሪትራዊው ይሥሓቅ ገብረ-ሥላሴ አንዱ ነበሩ።

ነፍሰ-ገዳዮቹ ባልና ሚስት ወዲያውኑ እዚያው የሳን በርናርዲኖ (San Bernardino) አውራጃ ውስጥ፣ ከፋሩቅ ቢሮ ብዙም ሳይርቅ ከፖሊሶች ጋር በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሲገደሉ፤ መክናቸው ውስጥ፣ እንዲፈነዳ አዘጋጅተው አሻንጉሉት ውስጥ ያስቀመጡት ቦምብ ነበርና፣ አደጋ ሳያደርስ በቶሎ ተደርሶበት መክኗል።

ይህ ግድያ የዩናይትድ ስቴትስ ሙስሊም ማኅበረሰብን በእጅጉ አሳስቧል፣ አሳዝኗልም። እንደ ማንኛውም ሰው ልባቸው ደምቷል።

"ከዚህ ቀደምም ያየንው በመሆኑ፣ አሜሪካውያን ሙስሊሞችን ብዙ ያስጨንቀናል» የሚሉት፣ የአሜሪካ-እስላማዊ ግንኙነት ምክር ቤት ኃላፊ ኒሃድ አዋድ (Nihad Awad) ናቸው። "ቶሎ ብሎ ወደ ድምዳሜ የመድረሱን ሚክንያትና በሕይወታችን ላይ የሚያስከትለውን አንደምታም በውል እንረዳለን" ሲሉም ተናግረዋል።

ግድያው በተፈጸመ ማግስት ማለትም ሐሙስ ሙሉ ቀን የስልክ ጥሪ ሲያስተናግዱ እንደዋሉ የሚናገሩት አዋድ፣ «ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት ብንክ ሰላም ነው?» የሚል ነበር ከተጨነቁ ወላጆች የሚደርሳቸው ጥያቄ።

የረቡዕ ማታው ግድያ፣ ሁለት ጎራ የለዩ ጥያቄዎችን በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ቀስቅሷል፣ ሽብርተኛነትና የጦር መሣሪያ ቁጥጥር።

ፕሬዚደንት ባርክ ኦባማ፣ ጥብቅ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ማድረግን ሲያሰምሩበት፣ ሽብርተኛነትንም እንደ አንድ ነጥብ አንስተውታል።

ሰዎች በአንድ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲወስኑ፣ ቁጥጥር ባለማድረጋችን ዕቅዳቸውን በቀላሉ እንዲያሳኩ ፈቀድንላቸው ማለት ነው።
ፕሬዚደንት ባርክ ኦባማ

ሌሎች ዲሞክራቶችም ይህንኑ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ወይም ገደብ የማድረግ ጥሪን ያጎሉታል። በመወሰኛው ምክር ቤት የአናሳዎቹ አባላት መሪ ሔሪ ሪድ (Harry Reid) በበኩላቸው "ምንም ያለማድረጋችን፣ ምንም ርምጃ ያለመውሰዳችን ነገር አሳሳቢ ነው። የዚህች አገር የህግ አውጪው ክፍል አባላት ሆነን ግን ምንም አናደርግም" ብለዋል ።

ሌላም፣ በምክር ቤቱ የአናሳው ወገን መሪ ናንሲ ፔሎሲም፣ "ከእንግዲህ ዝምታ አያስፈልግም። ሰዎች ባዘኑበት ጉዳይ ላይ ምንም ነገር ሳናደርግ ዝም ማለት እንደምን ትክክል ያደርገናል?" ብለዋል።

የሬፓብሊካኑ ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ ተፎካካሪዎች ግን፣ ግድያውን የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። እጩ ተወዳዳሪው ሴናተር ቴድ ክሩዝ "ግድያው ሌላው የሽብርተኛነት መገለጫ በመሆኑ ሁላችንንም ከልብ አሳዝኖናል። እዚሁ አገራችን ውስጥ የተፈጸመ ሌላው አክራሪነትና እስላማዊ ሽብርተኛነት" ብለው አክለዋል።

ሰኔተር ሊድዚ ግራም (Senator Lindsey Graham) ሌላዋ ለፕሬዚደንትነት የሚፎካከሩት የሬፓብሊካን ፓርቲው ዕጩ ናቸው። በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ ሲገልጹ "ባለፈው ረቡዕ የሆነው ከጦር መሣሪያ ቁጥጥር ወይም እገዳ ጋር የተገናኘ አይደለም። የአሸባሪነትና የነውጠኛነት ርዕዮተ-ዓለም በመላው ዓለም እየተስፋፋ የመሄዱ አካል እንጂ' ብለዋል።

ብዚዎቹን፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ፕሬዚደንታዊ ተወዳዳሪ ሂለሪ ክሊንተንን ጨምሮ፣ ግድያው በሙስሊም አሜሪካውያን ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ አሳስቧቸዋል። ብዙዎቹ ሙስሊም አሜሪካውያን፣ እንደማንኛውም ሰው ግድያው አሳዝኗቸዋል፣ አስስቧቸዋል።

ይህን የሁለት ወገን ክርክርና ጥያቄ በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት መርማሪዎች ተጨማሪ መረጃዎችን እያሰባሰቡ መሆናቸው ታውቋል።

አዲሱ አበበ ቀጣዩን ዘገባ አጠናቅሮ አቅርቦታል ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

የሳን በርናርዲኖ ግድያና የጦር መሳርያ ቁጥጥር በአሜሪካ እያከራከረ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:50 0:00

XS
SM
MD
LG