በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ደቡብ አፍሪካ የሰፋ ሚና እንድትጫወት ሂላሪ ክሊንተን ጠየቁ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን - ደቡብ አፍሪካ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን - ደቡብ አፍሪካ

የሦሪያው ባሻር አል አሣድ በቅርቡ እንደሚወድቁ የዩናይትድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተንብየው የሽግግር ዕቅድ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

(ይህ ገፅ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ኮምፕዩተርዎ ከአንድ በላይ ድምፅ ማጫወቻ አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ፅሁፍ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸው፡፡)

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸውን ዛሬ - ረቡዕ ነሐሴ 2/2004 ዓ.ም ለዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰጡት ንግግር አጠናቅቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውን የፀረ-አፓርታይድ ንቅናቄው የግንባር መሪ ሲሉም አወድሰውታል፡፡

ሃገራቸው ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብቶችን በዓለም ዙሪያ ለማበረታታትና ለማስፋት የሚያስችል ሰፊ ሚና ትጫወት ዘንድ ደቡብ አፍሪካዊያን የኔልሰን ማንዴላን ውርስ አንስተው በእርሣቸው ፈለግ እንዲራመዱም ሚስ ክሊንተን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሶሪያውን ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎችም ባለሥልጣናት ከመንግሥቱ ማፈንገጥና በአሌፖ የተጠናከረውን ውጊያ ተከትሎ የባሻር አል አሣድ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ ሊከተል ስለሚችለው ሁሉ ዕቅድ ማውጣት አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት ፕሪቶሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር አሣስበዋል፡፡

“የደቡብ አፍሪካን ዕጣ ፈንታና በዓለም ውስጥ የሚኖራትንም ሥፍራ መወሰን የእናንተ ጉዳይ ነው” ብለዋቸዋል ሚስ ክሊንተን ኬፕ ታውን ውስጥ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንግግር ሲያደርጉ፡፡

“ደቡብ አፍሪካ ወደፊት ትራመድ ወይም ወደ ኋላ ትቅር - የምትወስኑት እናንተ ናችሁ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በዓለምአቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ከፋፋይ የሆኑ አሮጌ መስመሮችን ትደመስስ ዘንድ የምትወስኑት እናንተ ናችሁ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ያረጁ ጥርጣሬዎችንና ቀልቦችን አስወግዳ የሃያ አንደኛው መቶ ክፍለዘመንን ፈተናዎች የሚመጥንና መጋፈጥ የሚያስችል አዲስ ዓይነት አጋርነትን ታነሣ ዘንድ የምትወስኑት እናንተ ናችሁ፡፡” አሉ ክሊንተን፡፡



ደቡብ አፍሪካ አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የምትከተላውን ስልቶች ለማስተዋወቅና ድጋፍም ለመሻት ያካሄዱት የአሥራ አንድ ቀናት የአህጉሩ ጉብኝታቸው ማዕከላዊ ትኩረት መሆኗን ክሊንተን በጉብኝታቸው መጀመሪያ ላይ ተናግረው ነበር፡፡ እነዚያ የአሜሪካ ስትራተጂዎች ሠላምን፣ ዴሞክራሲን፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበርንና የምጣኔ ኃብት ዕድገትን ከፍ አድርገው ካነሱና ከሚያጠናክሩ ሃገሮች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረቱ ወዳጅነቶችና ሽርክናዎችን ማበረታታትና ማስፋፋት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

“ለአፍሪካ ችግሮች የሚያስፈልጉት አፍሪካዊ መፍትሔዎች ናቸው እየተባለ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ፡፡ አሁን ማለት የምፈልገው ግን አንዳንድ የዓለማችን ችግሮችም አፍሪካዊ መፍትሔዎች እንደሚያስፈልጓቸው ነው፡፡ በዚህ አህጉር ውስጥ ደቡብ አፍሪካ የተሸከመችውን ያህል ክብደት መሸከም፣ የደቡብ አፍሪካን ያህልም ውጤታማ አጋር መሆን እና የመሪነት ሚና መጫወት የሚችሉ ሃገሮች ጥቂት ናቸው፡፡” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ፡፡

“ደቡብ አፍሪካ - አሉ ክሊንተን አክለው - በሌሎች ሃገሮች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት ከሚያስጨንቋቸው በዓለማችን ደቡብ ከሚገኙ ብዙ ዴሞክራሲዎች አንዷ ነች፡፡ ሆኖም የትም፣ በምንም ሥፍራ ሰብዓዊ መብቶች ሲረገጡ፣ ዴሞክራሲ፣ እውነተኛው ዴሞክራሲ ሲረገጥ፣ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ለማገዝ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሣደር እንዳለበት ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ይህንን ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ በላይ ሊረዳ የሚችል ማንም የለም፡፡”

ኒኩሊየር የጦር መሣሪያዎችን ላለመያዝ በራሷ ፈቃድ የወሰነች የመጀመሪያ ሃገር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ኢራን እየገፋችበት ነው ያሉትን ኒኩሌር የጦር መሣሪያ የመያዝ እርምጃ ለማስቆም እና የኒኩሌር ቁሣቁስ በሽብርተኞች እጅ እንዳይገቡ ለመከላከል እንዲቻል ግፊት ለማሣደር ከፍ ያለ ሚና እንድትጫወት ሂላሪ ክሊንተን ጠይቀዋል፡፡

“ኒኩሌር የጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ የደካማነት ሣይሆን የጥንካሬ ምልክት መሆኑን እናንተ ከማንም በላይ በሚያሣምን ሁኔታ መናገር ትችላላችሁ፡፡ በተጨማሪም ኒኩሌር የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት የሚጥር ማንኛውም ሃገር በራሱ ላይ የሚጋብዘው የበለጠ ጫናና መገለልን እንደሆነም በማሣመን በኩል እናንተ ማገዝ ትችላላችሁ፡፡” ብለዋል አሜሪካዊቷ ሚኒስትር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሚስ ክሊንተን ፕሪቶሪያ ላይ ትናንት ባደረጉት ንግግር የሦሪያው ፕሬዚዳንት የባሻር አል አሣድ ቀኖች የተቆጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይም የደም መፋሰስን ማቆምና ለፖለቲካ ሽግግር መዘጋጀት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“አሌፖ ውስጥ የተጠናከረው ውጊያና የሚታየው የመንግሥት ሰዎች ማፈንገጥ የሚያረጋግጥልን ተሰብስበን ጥሩ የሽግግር ዕቅድ የማውጣታችን ጉዳይ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ መጭው ምን ሊሆን እንደሚችል አገዛዙ በወደቀ በማግሥቱም መነጋገርና ማቀድ መጀመር እንችላለን፡፡ የጊዜ ገደብ እያስቀመጥኩ አይደለም፡፡ ልተነብየው የምችለውም ጉዳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ታዛቢዎች እንደሚረዱት ሁሉ እኔም ይህ ነገር እንደሚሆን እገነዘባለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

ክሊንተን ለመንግሥትም ለአማፂያኑም እንዲህ ሲሉ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አሰምተዋል፡፡

“የመንግሥቱ ተቋማት በሥራ ላይ መቆየት እንዳለባቸው ማረጋገጥ አለብን፡፡ የሃይማኖትና መሰል የመከፋፈል ግጭቶች ለማስወገድ የሚያስችሉ ግልፅ መልዕክቶችን ማስተላለፋችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡ በእጅ እዙርም ይሁን የሽብር ተዋጊዎችን በማሠማራት በሶሪያ ሕዝብ ሰቆቃ ለመነገድ የሚፈልጉ ሁሉ ግን ከማንም በፊትና በቅድሚያ በሦሪያ ሕዝብ ዘንድ በትዕግሥት እንደማይታለፉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡”

ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገው የዩናይትድ ስቴትስና የደቡብ አፍሪካ ሁለተኛው ስትራቴጂያዊ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን እየተባባሰ በመጣው የሦሪያ ቀውስ ጉዳይ ደቡብ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ የዩናይትድ ስቴትስን አቋም እንድትደግፍ ግፊት እንደሚያደርጉ ቀድሞም ተጠብቆ ነበር፡፡

ደቡብ አፍሪካና ዩናይትድ ስቴትስ በግጭቶች ውስጥ በማለፍና ከጭቆና በመውጣት ታሪኮቻቸው ጥልቅ እና የሚገዙባቸው ግንኙነቶችን የሚጋሩ ሃገሮች ናቸው - ብለዋል ክሊንተን፡፡

ክሊንተን የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸውን የጀመሩት የነፃነት ተዋጊውንና የቀድሞውን የሃገሪቱን ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን ቁኑ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያቸው ተገኝተው በመጎብኘት ነበር፡፡

ዛሬ ያደገጉትን ንግግር የጀመሩትና የቋጩት የአሁኑ የ94 ዓመት አዛውንት ማንዴላ የመጀመሪያው ድኅረ አፓርታይድ ፕሬዚዳንት ሆነው ሥልጣን ለያዙበት ሥነ-ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ ያደረጉትን ጉዞ በማስታወስ ነበር፡፡

ደቡብ አፍሪካ ለሰው ልጅ ክብር፣ በሃገር ውስጥ ብቻ ሣይሆን በውጭም ስላሉ የሰው ልጅ ዕድሎችና ዕጣ ፈንታ የኔልሰን ማንዴላን የትግል አርአያ እንድትከተል ጥሪ አሰምተዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከዚህ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸውና የሚጫወተውን እንደገና ያስጀምሩት፡፡ )


XS
SM
MD
LG