በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኃይለማርያም ደሣለኝ አንድ ዓመት


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ዛሬ ቃለ መሃላ ፈፀሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ዛሬ ቃለ መሃላ ፈፀሙ




please wait

No media source currently available

0:00 0:06:11 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የመለስ ዜናዊን ዕረፍት ተከትሎ ኃይለማርያም ደሣለኝ በቦታው ከተተኩ እነሆ አንድ ዓመት ሊደፍኑ ነው።

በቅርብ ጊዜያት የተቃውሞ ሰልፎች እንዲሁም የካቢኔ አባላት ብወዛ የተካሄደ ቢሆንም በምሥራቅ አፍሪካዊቱ ሀገር ብዙም የተለወጠ ነገር ያለ አይመስልም ብላለች የቪኦኤዋ ማርቴ ፋን ደር ቮልፍ ከአዲስ አበባ በላከችው ዘገባ።

ባለፈው ዓመት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን መታመም ተከትሎ ስለነበሩበት ሁኔታ ለሣምንታት በግምትና በጭምጭምታ ሲወራ ሰንብቶ ነኀሴ አሥራ አምስት ጠዋት የዕረፍታች መርዶ ተነገረ።
የኒህን የረጅም ጊዜ መሪ ዕረፍት ተከትሎ ነው ምክትላቸው የነበሩት ኃይለማርያም ደሣለኝ በህዝቧ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ የሆነቸውን ሀገር መሪነት ለመያዝ የተተኩት።

እርግጥ በቅርብ ወራት በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ በርካታ የመንግሥት ተቃዋሚ ሰልፎች ተካሂደዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም አብዛኞቹን የካቢኔ አባላት ቀይረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚሉት ግን እነዚህ ክስተቶች በመንግሥቱ ውስጥ የአንዳችም መሠረታዊ ለውጥ አካል አይደሉም።

“ባሁኑ ወቅት ኃይለማርያም እያደረጉ ያሉት በገዥው ፓርቲ የፀደቁ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ ነው። የአቅጣጫ እና የመሠረታዊ ፖሊሲ ለውጥ ይኖራል ብለው የሚጠብቁ ካሉ በርግጥ ያዝናሉ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማካሄድ ፍላጎቱም፣ ዝንባሌውም የለም” ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡

በምህንድስና የሠለጠኑት ኃይለማርያም ደሣለኝ እስከ አምና ነኀሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። እርሣቸው በጠቅላይ ሚኒስርነት መንበር ከተሰየሙ ወዲህ የጋርዮሽ ወይም የቡድን አመራር ሠፍኗል። የመንግሥቱ ባለሥልጣናት ግን “የቡድን አመራር የገዢው ፓርቲ ፖሊሲ ሆኖ የኖረ ነው” በማለት ይከራከራሉ።

በፀጥታ ጥናቶች ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ሰሎሞን ደርሶ “የፖለቲካ ሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትር እጅ መከማቸቱ ቀርቷል” ይሉና ቢሆንም ይህ የሀገሪቱን የፖለቲካ ገፅታ የመቀየሩን ነገር ይጠራጠራሉ።
አቶ ሰሎሞን ይቀጥሉና “የሚቀይረው ነገር ቢኖር በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተለያዩ የሥልጣን ማዕከሎች ወይም አካላት መካከል ውሣኔ አሰጣጥ ላይ የሚደረገውን ድርድር ወይም ክርክር ነው። የክልል መንግሥታት ጠንከር ያለ ቦታ እየያዙ መምጣታቸው ይስተዋላል። የኅብረቱ አባላት አሉ፤ በርግጥም ደግሞ የፀጥታው ተቋምም አለ። ስለዚህ የሀገሪቱን አመራር በሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በግልፅ እነዚህ የተለያዩ የሥልጣን ማዕከሎች መደራደር አለባችው ማለት ነው።”

ግርማ ሠይፉ በቅርብ ሣምንታት የተቃውሞ ሠልፎችን ካደራጁት ፓርቲዎች አንዱ ከሆነው ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብቸኛው ተቃዋሚ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በፓርላማው ውስጥ ያላቸው ባህርይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ቀድሞ ሁሉም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበሩ። ማለትም የሀገሪቱ ህግ እርሣቸው ነበሩ። ስለዚህም ፓርላማው ምንም ፋይዳ አልነበረውም” ብለዋል፡፡

ይህን ያሉት ግርማ ሠይፉ ያስከትሉና በሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስሮች መካከል የምግባር ልዩነት ቢኖርም የኢትዮጵያ መንግሥት የተለየ አመለካከት ላላቸው ሰዎች የበለጠ ነፃነት መስጠት ላይ ያለው አቋም እንዳልተቀየረ ነው የሚሰማቸው።

“በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ለመቀየር አንድ የሚታይ ርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ሁኔታዎችን ክብደት ሰጥተው በማጤን መሻሻል የሚችልበትን እርምጃ መውሰድ አለባቸው። የኢኮኖሚ ልማትና መሠረተ ልማት ብቻቸውን የሰብዓዊ መብቶችን ጉድለቶች ሊሞሉ አይችሉም” ብለዋል እንደራሴ ግርማ ሠይፉ፡፡

ኢትዮጵያ 1983 ዓ.ም ጀምሮ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት በሆነው በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ስትመራ ቆይታለች፡፡ መለስ ዜናዊም እስከ ዕለተ ሞታችው ድረስ የግምባሩ መሪ ነበሩ። ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሣለኝ በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው የፊታችን ምርጫ ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ላይ ባሣለፉት በዚህ በመጀመሪያው ዓመታቸው በጣም ጎልተው ባይታዩም ቃል አቀባያቸው ጌታቸው ረዳ እንደሚሉት ግን ሁለተኛው ዓመት ከዚያ የተለየ ይሆናል።

አቶ ጌታቸው ስለመጭው ጊዜ ሲናገሩ “ከአመራራችው መጠበቅ የሚቻለው ከህዝቡ ጋር ይበልጥ የተቀራረበ ግንኙነት እንደሚኖራቸው፤ለዲሞክራሲው ሂደት መጠናከር እና ለምጣኔ ኃብቱ ዕድገትም የበለጠ ተራማጅ አመለካከትና አቋም እንደሚይዙ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የመንግሥቱ አኀዛዊ መረጃ እንደሚያሣየው ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአሥር ከመቶ በላይ የወጣ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ እርግጥ የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዕድገቱ ወደ ስምንት ከመቶ ገደማ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ሀገሪቱን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2025 ከባለመካከለኛ ገቢ ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የታለመውን ግዙፉን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ የማድረጉ ሂደትም ተጋምሷል።

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG