በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በጦር ኃይሏ በጥቁር አፍሪካ ‘አንደኛ’ ነች


የኢትዮጵያ ጦር ሰልፍ
የኢትዮጵያ ጦር ሰልፍ

የዓለምን የጦር አቋም የሃገሮች ደረጃ የሚያወጣው “ግሎባል ፋየርፓወር” ዌብሣይት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከሰሃራ በስተደቡብ ባለው አፍሪካ እጅግ ብርቱው መሆኑን አስታውቋል፡፡


የጦር ግንባር
የጦር ግንባር
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:16 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የዓለምን የጦር አቋም የሃገሮች ደረጃ የሚያወጣው “ግሎባል ፋየርፓወር” ዌብሣይት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከሰሃራ በስተደቡብ ባለው አፍሪካ እጅግ ብርቱው መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር አቋም ከደቡብ አፍሪካ፤ ከናይጀሪያና ከኬንያም ኃይሎች እንደሚያይል ዌብ ሣይቱ አመልክቷል፡፡

“ግሎባል ፋየርፓወር” የስያሜው ቃል በቃል ትርጉም “የዓለም የተኩስ አቅም” ወይም “የዓለም የጦር አቋም” ሊሆን ይችላል - ኢትዮጵያ በጦር ኃይሏ ብርታት በዓለም አርባኛ መሆኗን አሣይቷል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያን ተከትላ በዓለም 41ኛ ነች፡፡ ናይጀሪያ 47ኛ፣ የኢትዮጵያዋ ጎረቤት ኬንያ ደግሞ 63ኛ ነች - በጦር ኃይሎቿ ጥንካሬ፡፡

በጥናቱ ውስጥ ከታቀፉት 106 የዓለም ሃገሮች መካከል ኤርትራ የለችም፡፡

አጠቃላዩን የአፍሪካን አቋም የዳሰሰው ይኸው የ “ግሎባል ፋይርፓወር” ሪፖርት በአፍሪካ እጅግ ኃያል የሚለው የግብፅን ጦር ነው፡፡ በዓለም በ13ኛ ብርቱ ተብሎ የተመዘገበ ነው፡፡ የግብፅ ጦር በሰሌዳው ላይ የሠፈረው ነባር ከሚባሉት የአካባቢ ኃይሎች፣ ከፓኪስታን፣ ከብራዚል፣ ከጣልያንና ከእሥራኤል ጋር መሣ ለመሣ በሆነ አንድ ሰልፍ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጦር
የኢትዮጵያ ጦር
ይህ ስለ ዓለም የኃይል ሚዛን አንፃራዊ የሆነ ግንዛቤ ያስጨብጣል የተባለ የግሎባል ፋየርፓወር የጦር ብርታት ደረጃ የወጣው በዌብ ሣይቱ ባልደረቦች በተሰባሰቡ፣ በተጠናቀሩ፣ በተጠኑና በተተነተኑ ማንም ሊያገኛቸው በሚችል መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡

ለመሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ የዛሬ የኃይል ሚዛን ምን ይመስላል? ፒተር ሃይንላይን ለንደን በሚገኘው የስልታዊ ጥናቶች ዓለምአቀፍ ኢንስቲትዩት ወታደራዊ ተንታኝ እና በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ ገፅታ ባለሙያ ወደሆኑት ጄምስ ሃኬት ደውሎ ጠይቋቸው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የጦር ኃይሎቿን በዘመናዊ ሁኔታ ለማደራጀትና ለማስታጠቅ እጅግ የሚያስደንቁ እርምጃዎችን ማድረጓንና የበለጠው ትኩረቷ የበረታው ደግሞ ብዙ ትጥቅና ሠራዊት የተኮለኮሉባቸው ባሉት ከኤርትራ ጋር በምትዋሰንባቸው ድንበሮቿ ላይ መሆኑን ሃኬት ገልፀዋል፡፡

“ጦሩን በዘመናዊ አቋም የማደራጀቱ ሥራ በሰው ኃይልም በመሣሪያም ላይ ያተኮረና ሥፋት ያለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ቲ-72 ግዙፍ የፍልሚያ ታንኮችና ኤስዩ-27 ዓይነት ተዋጊ ጄቶችን በመሣሰሉ ዘመናዊ አቅም በሚሰጡ መሣሪያዎች ተጠናክራለች፡፡ የጦር ሠራዊቷ ቁጥር ግን ኤርትራ ድንበር ላይ የሠፈረውን ኃይሏን መሸፈን በሚችል ሁኔታ ላይ አተኩሮ 135 ሺህ ነው፡፡ ለሃገር ውስጥ ፀጥታዋ ቅድሚያ ብትሰጥም ድንበር ዘለል ለሆኑ የተራዘሙና በመካሄድ ላይ ያሉ ዘመቻዎችም ወታደሮችን ታሠማራለች፡፡ ይህ ሁኔታ ከበድ ያለ ፈተና የሚደቅንባት ቢሆንም ረዥም ዕድሜ ካስቆጠረው በአህጉሪቱ ሠላም ማስከበር እንቅስቃሴዎች ተሣትፎዋ ባካበተችው ልምድ ይህንን ችግር እንደአመጣጡ ለመያዝ ችላለች” ብለዋል ሃኬት፡፡
የጦር ግንባር
የጦር ግንባር
ይህ የግሎባል ፋየርፓወር ዌብሣይት ደረጃ አመዳደብ ቀልብን የሚስብ ቢሆንም - አሉ ሃኬት - በአጠቃላይ ወታደራዊ አቋም ግን ኢትዮጵያ ዘንድሮ በውኑ ከደቡብ አፍሪካ አይላለች ብሎ ለመደምደም ይከብዳል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የጦር ኃይሎች ሌሎቹ ሃገሮች በሌሏቸው ከባድ ትጥቆች የተደራጁ ዘመናዊ ኃይሎች መሆናቸውን፤ የናይጀሪያ ጦር በአንፃራዊ ሁኔታ ዘመናዊ የሆነና አሁንም በዘመኑ ደረጀ እየታጠቀ ያለ መሆኑን ሃኬት ገልፀዋል፡፡ “በአካባቢ ደረጃ ስናየው እርግጥ ነው፤ በአንፃራዊ መልኩ የኢትዮጵያ ጦር ኃያሉ ነው” ብለዋል፡፡ ነገር ግን - አክለውም - “በቅርብ ዓመታት ውስጥ ደግሞ የኬንያም ጦር እየተጠናከረ እየመጣ ነው፡፡ ዩጋንዳም ዘመናዊ ትጥቅና አቋም ያላት ሃገር ነች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን በአካባቢ ደረጃ በአንፃራዊነት የበለጠች ኃይለኛ መሆኗን መናገር ይቻላል፤ በአህጉር ደረጃ ግን የጦር ኃይሏ እጅግ ኃይለኛው ነው አስቸጋሪ ነው” ብለዋል፡፡

ግሎባል ፋየርፓወር በጥናቱ ውስጥ ኤርትራ እንዳልተካተተች ነው የተናገረው፡፡ ጄምስ ሃኬት ግን የኤርትራ ጦር ደረጃ ዝቅ ተደርጎ መታየት የሌለበት ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም የኤርትራ ታንከኛ ጦር በዕድሜ ከኢትዮጵያውም እንደሚበልጥ፤ አሥመራ አየር ኃይሏን በቅርቡ ዘመናዊ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

“የምድር ጦርን በተመለከተ፤ ኤርትራ ውስጥ የምናየው በአጠቃላይ አገላለፅ በዕድሜ የበለጠ መሆኑን ነው፡፡ ጥቂት ቢሆኑም ከሁሉም የቆየ የሚለው አባባል የጠላትን ማንነት ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ቁጥሩ ዕጥፍ የሆነ አቅም ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር የምታወዳድር ከሆነ ግን፣ የምትፈትሸው 200 ቲ-27 ዘመናዊ የሚባሉ የሩሲያ ሥሪት የሆኑ የውጊያ ታንኮችን ከሆነ ግን፤ ታሪኩ ስለራሱ የሚናገር ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ የኤርትራን አየር ኃይል የወሰድክ እንደሆነ ሚግ 29 የውጊያ ጄቶችን የታጠቀ እና በኤስዩ-27 የውጊያ ጄቶች የጥንካሬ ድጋፍ የሚያገኝ ነው፡፡ ስለዚህ የኤርትራ አየርኃይል ከሌላው የጦር ክፍሏ በተሻለ ሁኔታ ዘመናዊ እንዲሆን ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ሚግ-29 (ሩሲያ ሠራሽ)
ሚግ-29 (ሩሲያ ሠራሽ)

በሌላ በኩል ደግሞ የስልታዊ ጥናቶች ዓለምአቀፍ ኢንስቲትዩቱ ጄምስ ሃኬት አክለው እንደማስታወሻ በሰጡት ቃል ኢትዮጵያ የጦር ኃይሎቿ የጎሣ ስብጥር የሰፋ እንዲሆን ጥረት ማድረጓን ገልፀው በዚህም ምክንያት የትግራይ ጎሣ አባላት የሆኑ እጅግ ብዙ ወታደሮችን ማሰናበቷን አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባ የጦሩን የዘር እና የሃይማኖት ስብጥር ለማስፋት ይዛዋለች ያሉትን አካሄድ ሃኬት ቢያሞግሱትም ውጤቱ ምን እንደሚሆን ግን ዛሬ ላይ ሆነን ለመናገር “ጊዜው እጅግ ማለዳ” ነው ብለዋል፡፡ “ይህ ሥራ ገና በሂደት ላይ ያለ ነው” ብለዋል ሃኬት በዚሁ ለቪኦኤ በሰጡት ትንታኔአቸው፡፡
XS
SM
MD
LG