በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦሮሞ ተወላጆች ሰልፎች ዋሽንግተንና ለንደን ላይ ተካሄዱ


የኢትዮጵያ ኤምባሲ - ዋሽንግተን ዲ.ሲ
የኢትዮጵያ ኤምባሲ - ዋሽንግተን ዲ.ሲ

የኦሮሚያ ተማሪዎች እያሰሙ ስላሉት ተቃውሞና በፀጥታ ኃይሎች ስለተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:00 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ
please wait

No media source currently available

0:00 0:12:18 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የኦሮሚያ ተማሪዎች እያሰሙ ስላሉት ተቃውሞና በፀጥታ ኃይሎች ስለተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

“የኦሮሞ ገበሬዎችን በዘዴ ማፈናቀልና ግድያን ጨምሮ በተማሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ ይቁም” ሲሉ የጠየቁ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ዛሬ ዋሽንግተን ዲ.ሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ያሉት የጭካኔ የኃይል እርምጃ ነው ሲል የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውቋል፡፡

የዋሽንግተን ዲ.ሲ ሜትሮፓሊታን የኦሮሞ ወጣቶች ቡድን ያዘጋጀውና የመራው ሰልፍ ነው በኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጅ ላይ የተካሄደው፡፡

ሰልፈኞቹ “ኢትዮጵያ ውስጥ የተቃውሞ ድምፃቸውን እያሰሙ ካሉ ተማሪዎች ጎን እንቀማለን፤ የኦሮሞ ገበሬዎችን ማፈናቀልን፣ መንግሥት እያከናወነ ባለው ሥራ ላይ ትኩረት ስለሳቡ ጥቃት በተሠነዘረባቸው ተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን ጅምላ ግድያ እንቃወማለን” ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ወጣቶች ቡድኑ ከሰልፉ ጋር አያይዞ ያወጣው የፕሬስ መግለጫ “ሥጋታችንን እያሰማን ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ልቅ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣ፤ በተለይ በውጤቱ በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ገበሬዎችን ከአዲስ አበባ አካባቢ ሊያፈናቅል የሚችለውን የመንግሥት ዕቅድ በሰላማዊ መንገድ በተቃወሙ ተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ እየተከታተሉ እንዲዘግቡና እንዲያጋልጡ ለመገናኛ ብዙኃን ጥሪያችንን እናቀርባለን” ይላል፡፡

በኤምባሲው ደጅ ላይ የተካሄደውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው አቶ ዋህደ በላይ በተፈጠረው ሁኔታ መንግሥት በእጅጉ ማዘኑን በይፋ መግለፁን ሕይወታቸው ለጠፋ ሰዎች ቤተሰቦችም ይህንኑ ማሳወቁን ገልፀዋል፡፡

አቶ ዋህደ የሰልፉን መካሄድና ያዩትን በተለመደው አሠራር ወደ አዲስ አበባ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ አጎራባች የሆኑት የኦሮሚያ ከተሞች ወደ ርዕሰ ከተማይቱ ይካተታሉ የተባለው ግን “ስህተት ነው” ብለዋል፡፡ “መንግሥት ለተፈጠረው ሁኔታ ይቅርታ ይጠይቃል ወይ?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ዋህደ “ከዚያ በፊት ማጣራት እየተካሄደ በመሆኑ ውጤቱ መታየት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሂዩማን ራይትስ ዋች የሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ትናንት ናይሮቢ-ኬንያ ላይ ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያ ተቃውሞን በጭካኔ እየበተነች ነው” ብሏል፡፡

“የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እየገለፁ ባሉ ተማሪዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል እየተጠቀመ ነው - ብሎ - ባለሥልጣናቱ በዘፈቀደና በጅምላ ያሠሯቸውን በአፋጣኝ እንዲፈቱና ምርመራ እንዲከፈት፣ ጥፋተኞችም እንዲጠየቁ” አሳቧል፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ጉዳዮች እጥኝ ሆርን ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ “ያየነው ነገር የፀጥታ ኃይሎች በመላ ሃገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ያለተጠያቂነት ነው፡፡ ያጠፉ አይጠየቁም፡፡ እኛ ሶማሌ ክልል ውስጥ ከኦብነግ ጋር እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ የተሠራውን አድራጎት መዝግበናል፤ ሶማሊያ ውስጥም፣ ኦሮሚያ ውስጥም፣ እንዲሁም ጋምቤላ ውስጥም የፈፀሟቸውን አድራጎቶች መዝግበናል፡፡ ባለፈው ሣምንት ያየነው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የተፈፀሙ የጭካኔ እርምጃዎችን ነው” ብለዋል፡፡

“የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን ሕገወጥ አድራጎቶች የሚፈፅሙት ያለአንዳች ተጠያቂነት፤ አጥፍተው በነፃነት እየኖሩ ነው፡፡ ያጠፉ ተቀጥተው አያውቁም፡፡” ብለዋል ሆርን አክለው፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ የአፍሪካ አጥኝ አክለውም “የፀጥታ ባለሥልጣናቱ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት ወይም ከሕግ ጋር የተጣጣሙ ይሁኑ አይሁኑ የረባ ምርመራ አይካሄድም ወይም ጨርሶ ምርመራ አይደረግም - ብለው ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገሮች ኢትዮጵያ በእነዚህ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ላይ በነፃ አካል ፍተሻዎችን እንድታካሂድ ግፊት እንዲያሳድሩባት ቡድናቸው እየጎተጎተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህንን የምርመራና የተጠያቂነትን ጉዳይ አስመልክቶ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲው ቃልአቀባይ አቶ ዋህደ በላይ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “አንድ የውጭ የአድቮኬሲ ቡድን ለሚያቀርባቸው ክሦች መልስ መስጠት ብዙም አስፈላጊ አይመስለኝም፤ ይልቅ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የምርመራውን ሂደትም ሆነ የተጠያቂነት ጉዳዮችን እየተከታተለ ሊጠይቅ ይገባዋል” ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ዛሬ ለንደን ላይ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡

የሰልፉ አስተባባሪ ዶ/ር ግዛው ታሲሳ ለቪኦኤ ስለሰልፋቸው ዓላማ አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ግዛቸው ጥያቄዎቻቸው “የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ግድያ እየፈፀመ ያለው ከውጭ በሚያገኘው እርዳታ ስለሆነ እንዲቋረጥ፣ ካለበለዚያም እርዳታው በትክክለኛው ሥራ ላይ መዋሉን ለጋሾች ተከታትለው እንዲያረጋግጡ፤ ምርመራ እንዲከፈትና ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ፣ እኛ እንግሊዝ ውስጥ ሆነን የምንከፍለው ታክስ ለዜጎቻችን መፍጃ እንዳይውል” የሚሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “ባዶ እጃቸውን መሣሪያ ፊት ለቆሙ ተማሪዎች ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል” ብለዋል አስተባባሪው አክለው፡፡

በሌላ ዜና ደግሞ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ዛሬም የተማሪዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ደንቢ ዶሎ ከተማ፣ የቄለም ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሰልፍ ለመውጣት ሲሞክሩ በፖሊስ መከልከላቸውንና ክልከላውን አልፈው ለመውጣት ሲሞክሩም በተነሣው ግጭት አንዲት የ11ኛ ክፍል ተማሪ በጥይት እዷ ላይ መመታቷን ተማሪዎቹ ገልፀውልናል፡፡

እዚያው ወለጋ ውስጥ በቄለም ጨንቃ ከተማ ሊደረግ የነበረ ሰልፍም በፖሊስ ኃይል ተበትኖ ትምህርት ቤቱ መዘጋቱንም ተማሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ዛሬ ትምህርት የለም ተብሎ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ተነግሮን ስንመለስ አድማ በታኝ ፖሊስ ከመካከላችን ብዙዎችን አሠረ፣ የተደበደቡም አሉ፤ ሲሉ በበግዳ አያና ወረዳ የአያና ከተማ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ለተጨማሪ የላይ የተያያዘውን ዘገባ እና ከአቶ ዋህደ በላይ ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ ሙሉ ቃል የያዙትን የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG