በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በኤድስ ቁጥጥር እምርታ አደረገች


በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ሥርጭትና በኤድስ ሞት በሃያ ከመቶ መቀነሱ ተገለጸ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም - ዩኤንኤድስ ጋር በመተባበር ያወጣው የቅኝት ሪፖርት በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ሥርጭት መጠንና ከኤድስ ጋር የተያያዘ ሞት መቀነሱን ገለፀ።

ዓለምአቀፍ የኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ የወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቁጥጥር፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ላለ ዜጎች የሚደረግ ህክምና እንዲሁም ለታመሙ እንክብካቤ ካለፉት ዓመታት ጉልህ መሻሻል ማሳየቱን ገልጿል።

የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስቀሌ ሌራ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ እምርታ የተገኘበትን ምክንያት ሲገልፁ የኤችአይቪ ትልልፍ ከጠባይ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የህዝብን የአኗኗር ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችሉ እርምጃዎች እንደተወሰዱ ለምሳሌ ከዘጠና ከመቶ በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች ስለወረርሽኙ ውይይት እንደተካሄደና ህዝቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደተቻለ ተናግረዋል። የህዝቡ ግንዛቤ በጨመረ ቁጥር ደግሞ መገለልና መድሎ እንደቀነሰ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በየማኅበረሰቡ መስፋፋት ለኤችአይቪ ምርመራና ህክምና ሁኔታዎችን የበለጠ ማመቻቸቱን አስገንዘበዋል።

ኤችአይቪ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ ከእናት ወደ ልጅ ሲሆን በዚህ ረገድ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ የተወሰደ እርምጃ ለጊዜው እምብዛም ባይሆንም ለሚቀጥሉት ዓመታት በትኩረት ሊሠራበት መታቀዱን ጠቁመዋል። አቶ መስቀሌ ሌራ በኤችአይቪ/ኤድስ ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች የሚደረግ እንክብካቤም በኢትዮጵያ በመጭዎቹ ዓመታት የበለጠ ትኩረት እንደሚያገኝ አመልክተዋል።

ከኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስቀሌ ሌራ ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG