በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"የኢትዮጵያ ሕፃናትና ባሕር ዘለል ጉዲፈቻ" ክፍል አንድ


ባክነር/ብራይት ሆፕ ት/ቤት (ባንቱ/ኢትዮጵያ)
ባክነር/ብራይት ሆፕ ት/ቤት (ባንቱ/ኢትዮጵያ)

ድኃይቱ ሃገር በበረከተ የውጭ ወረት እየነቀዘ ባለው ማኅበራዊ መዋቅር ላይ ዐይኗን ስታሣርፍ

ኢትዮጵያ በአሥሮች የሚቆጠሩ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት ማሣደጊያዎችን ለመዝጋት እያቀደች መሆኑ ተነግሯል፡፡ ሃሣቡ ተቺዎቹ የሕፃናት ንግድ በሚሉትና እየተስፋፋ በመጣው በውጭ የጉዲፈቻ ተግባር ላይ ለተሠማሩ ወኪሎች ፍቃድ ማደስ ማቆምንም እንደሚያካትት ታውቋል፡፡

"ድኃይቱ ሃገር በበረከተ የውጭ ወረት እየነቀዘ ባለው ማኅበራዊ መዋቅር ላይ ዐይኗን ስታሣርፍ" ይላል አዲስ አበባ የሚገኘው ሪፖርተራችን ፒተር ሃይንላይን ያስተላለፈው ዘገባ፡፡

ለዚህ ዘገባ የኢትዮጵያ ሕፃናት ለውጭ አሣዳጊዎች የማሰጡበትን አሠራር የሚያከናውነው፣ የገንዘብ ምንጩ ቴክሣስ - ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ የዕምነት ተቋምና ግብረ ሰናይ ድርጅት የሆነ "ብራይት ሆፕ" (ብሩሕ ተስፋ) የሚባል ማዕከል ነው - ኤግዚቢቱ፡፡

በዚህ ማዕከል ውስጥ ዕድሜአቸው ከወራት እስከ አራት ዓመት የሆነ ሕፃናት ለአሣዳጊዎቻቸው እስኪተላለፉ በጥንቃቄ ተይዘዋል፡፡ ሃያ ሕፃናት - ለጊዜው "ከወላጆቻቸው ጋር ያልሆኑ?"፤ "ሰብሳቢ ያልነበራቸው?"፤ "የተጣሉ?" ብቻ ቃሉ ባይመችም ነገሩ እንዲሁ ነው፡፡ "አባንደንድ" ይላቸዋል ፒተር በእንግሊዝኛው፡፡

ከእነዚህ ሕፃናት አብዛኞቹ በዘመድ አዝማድ አሣዳጊ እንደሚወሰዱ የብራይት ሆፕ (ብሩህ ተስፋ) ማዕከሉ ዳይሬክተር ጌታሁን ነሲቡ ተሰማ ተናግረዋል፡፡

"ዋናው ዓላማችን - አሉ ጌታሁን - ሕፃናቱን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ማገዝ ነው፡፡ ጉዲፈቻ፣ በተለይ ደግሞ የባሕር ማዶው የመጨረሻው አማራጫችን ነው፡፡"

ከእነዚህ ጉዲፈቻን ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚያፈላልጉ ድርጅቶች ለሕፃናቱ የሃገር ውስጥ አሣዳጊ ለማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ብራይት ሆፕ (ብሩህ ተስፋ) የተለየ መሆኑን የፒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡ በዚህ በያዝነው ዓመት (እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓዊያኑ 2010 ማለት ነው) አምስት ሺህ የኢትዮጵያ ሕፃናት ለውጭ አሣዳጊዎች ይሰጣሉ፡፡ የእያንዳንዳቸው አሣዳጊዎች ታዲያ ለዚያ በመታደላቸው ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ሺህ ዶላር ይከፍላሉ፡፡ በዛሬ ምንዛሪ ከ335 ሺህ እስከ 418 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ ሕፃናት ገሚሱ - ምናልባት እስከ 2 ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑት የሚሄዱት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አሣዳጊዎች ነው፡፡ ይህ ቁጥር ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው በአሥር እጥፍ ያሻቀበ እንደሆነ ነው የሚሰማው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባሏ እና የተወካዮች ምክር ቤቱ (የኮንግረሱ) የጉዲፈቻ ጉዳዮች ሸንጎ ሊቀመንበር ሜሪ ላንድሩ በቅርቡ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ እግረ መንገዳቸውን ወደ ብራይት ሆፕ ጎራ ብለዋል፡፡ (በነገራችን ላይ በዚህ ዘገባ ውስጥ ፒተር ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር "የአሜሪካዊያን የባሕር ማዶ ጉዲፈቻ ቀልብ ማረፊያ" ነው የሚላት፡፡)

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በአሣዳጊዎች የሚወሰዱ ሕፃናት ቁጥር እንዲህ ሽቅብ የተተኮሰበትን ምክንያት "ለማስተዋል እኮ ቀላል ነው" ይላሉ ሴናተር ላንድሩ፡-

"ከምክንያቶቹ አንዱ የአሜሪካ ሰዎች በኢትዮጵያዊያን ሕፃናት በፍቅር የመውደቃቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይወዷቸዋል፡፡ ነገሩ ቀላል ነው፤ ቆንጆዎች፣ ንፁህና ንቁ ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡" ብለዋል፡፡

ይህ የኢትዮጵያዊያን ጉዲፈቻ እንዲህ ፈጥኖ ማሻቀብ ግን በሕፃናት መብቶች ተሟጋቾች ዘንድ የማንቂያ መሰል ደወል እያንጫረረ ነው ይባላል፡፡

የዩናይትዩ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ከጉዲፈቻ ጋር የተያያዙ የማጭበርበር አድራጎቶችን፣ በአንዳንድ ባለሥልጣናትም ዘንድ ለሥነ-ምግባርና ለሕግም የማይመች መመሣጠርን፣ የሕፃናቱንም ደህንነት የሚጎዱ ተግባራትን መነሻ ያደረጉ ሥጋቶቹን የጠቋቆመበትን መግለጫ በቅርቡ አውጥቶ ነበር፡፡

የወደፊት አሣዳጊዎች በዚህ በጉዲፈቻው አሠራር አፈፃፀም ላይ መዘግየት ሊኖር እንደሚችል እንዲያውቁ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው አሣስቦ ሕፃኑ "ሰብሳቢ አጥቷል" በተባለባቸው ምክንያቶችና ለሌላ አሣዳጊ በመስጠቱ አስፈላጊነት ላይ ውሣኔ ለመስጠት ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡

ሕፃኑ "ወላጁን ያጣ" የሚለውን በዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን ሕግ ላይ የሠፈረውን ትርጓሜ ያሟላ እንደሆነም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡

ያልተለመደ የጉዲፈቻ ተግባር በማስፈፀም አድራጎት ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችና ወኪል ድርጅቶችን ነጥሎ ለማወቅ የሁለት ዓመታት የመረጃ አሰባሰብና ክትትል ሥራ እንደጠየቃቸው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኮንሱላር ክፍል ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡

በድህነት ውስጥ በምትገኝ ሃገር ሰዎቹ የሚጨባበጡባቸው ተረፍረፍ ያሉት የጉዲፈቻ ገንዘብ እጆች በእጅጉ የሚያማልሏቸው መሆኑን በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ተጠሪ ዳግ ዌብ ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ አሉ፡፡ "በዚህች ሃገር ውስጥ ገንዘብ ኃይለኛ ነገር ነው፡፡ የምንነጋገረው በአንድ ጉዲፈቻ ወደ ሃገሪቱ ስለሚገባ ሃያ ሺህና ሃያ አምስት ሺህ ዶላር ነው፡፡ በዚያ ላይ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ ችግሮች አሠራሮች ውስጥ ያሉ የተበላሹ አድራጎቶች ማሣያዎችም እየጨመሩ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ በፒር ተመዝግበው ተይዘዋል፡፡"

ፒር - ወላጆች ጨዋነት ለተመላው የጉዲፈቻ አሠራር ማሻሻያ (PEAR - Parents for Ethical Adoption Reform) የተባለ ቡድን የእንግሊዝኛው መጠሪያ ምሕፃር ነው፡፡ ፒር ታዲያ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ያ ጥናት የተደረገው የቪየትናምና የጓቲማላን ሕፃናት ለአሜሪካዊያን አሣዳጊዎች የሚሰጠው መርኃግብር በሁለቱ ሃገሮች ውስጥ ከመዘጋቱ በፊት ይታዩ የነበሩ አንዳንድ የችግሮች ተመሣሣይ ልማዶች ረድፎች በመስተዋላቸው ነበር፡፡ ይህ የፒር ጥናት እነዚያ የጉዲፈቻ ድለላ ወይም አስፈፃሚ ድርጅቶች እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን አሣልፈው እንዲሰጡ የሚያስገድዱባቸውን ሥነ-ምግባር የጎደላቸው ክፉ ተግባራት ማስረጃዎችን መሰብሰብና ማጋለጥ ችሏል፡፡

ወላጆቻቸውን ባጡ ሕፃናት ማሣደጊያዎቸ ውስጥ ያለው የኑሮ ሁኔታ የተበላሸ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሚፈስ ወይም የሚወርድ ንፁህ ውኃ የላቸውም፡፡ እንዳንዶቹ ደግሞ ከናካቴውም የንፅህናና የመፀዳጃ ቦታዎች የሏቸውም፡፡ በአንዳንዶቹ ሕፃናት ላይ የወሲብ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸው፤ እንደሚደበደቡም ጥናቱ ያሣያል፡፡

ይህንን የፒር ጥናት ውጤት የራሣቸውም ጥናት ውጤት እንደሚያጠናክርና እንደሚያረጋግጥ የኢትዮጵያም ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ የሕፃናት መብቶች ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተር ማኅደር ቢተው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል ከቅድሚያዎቻቸው የሚቀድመው እነዚያን የሕፃናቱን ደህንነትና መብቶች የማይጠብቁ በአሥሮች የሚቆጠሩ "ወላጅ ያጡ ሕፃናት ሕፃናት ማሣደጊያ" የሚባሉትን ተቋማት መዝጋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

"ከስድስትና ከሰባት ዓመታት በፊት አሁን ያሉትን ያህል ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት ማሣደጊያዎች አልነበሩም - ይላሉ ዳይሬክተር ማኅደር ቢተው - የጉዲፈቻዎቹ ድርጅቶች ቁጥር ሲጨምር የሕፃናት ማሣደጊያዎቹም ቁጥር አብሮ አሻቀበ፡፡ ከእነዚህ ማሣደጊያዎች የሚበልጡቱ ማሣደጊያ አይደሉም፡፡ የማሸጋገሪያ ኬላ ናቸው፡፡ ሕፃናቱን ይቀበላሉ፤ ለጉዲፈቻ ይሰጣሉ፡፡ ማስተላለፊያ ቦይ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ማሳደጊያዎች አያስፈልጉንም፡፡"

እነዚህ በዩናይትድ ስቴትስና በአውሮፓም ያሉ ጥቂት አሣዳጊዎችን ፍላጎት ለማሟላት የተቋቋሙ ማሣደጊያዎች የሚዘጉበትን ጊዜ ማኅደር አልገለፁም፡፡ በርግጥ በሺሆች የሚቆጠሩ ከተቋማቱ ውጭ የሚሆኑ ሕፃናትን ባለሥልጣናቱ ቦታ ቦታ እስኪያስይዟቸው ከማሣደጊያዎቹ 25 ከመቶ የሚሆኑት በቅርቡ ሲዘጉ መጠነኛ መረበሽ ሊፈጠር እንደሚችል ዳይሬክተሯ ያምናሉ፡፡

ይሁን እንጂ የገንዘብ ማማለያው ሲቋረጥ ሃገር አቋራጭ ለሆነው ጉዲፈቻ ጉዳይ የሚጎርፉት ሕፃናት ቁጥርም ይቀዘቅዛል ብለው ያስባሉ - ማኅደር፡፡

እነዚያን በተበላሸ አሠራር ውስጥ የገቡ ድርጅቶችን ለቅሞ ለማውጣትና ለመጣል እንዲቻልም በባሕር ዘለል ጉዲፈቻ ሥራ ላይ የተሠማሩ ድርጅቶችን ሁሉ ፍቃድ መንግሥት እንደገና እንደሚያድስ ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትኩረት የሕፃናት ደህንነት ተሟጋቾች ለዓመታት ሲወተውቱና ሲጎተጉቱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

"የኢትዮጵያ ሕፃናትና ባሕር ዘለል ጉዲፈቻ" ዘገባ "ክፍል አንድ" ን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG