በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተመስገን ደሣለኝ ጤና


ተመስገን ደሣለኝ
ተመስገን ደሣለኝ

የፍትሕና ልዕልና ጋዜጦች፣ እንዲሁም የፋክትና የአዲስ ታይምስ መፅሔቶች ባለቤትና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ከታሠረ ፤ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም አንድ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ የተመስገን ጤና አሳሳቢ መሆኑን ቤተሰቦቹ ገልፀዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ግን ተመስገን ሕክምና እያገኘ መሆኑንና ጤናማም እንደሆነ ይናገራል፡፡

የፍትሕና ልዕልና ጋዜጦች፣ እንዲሁም የፋክትና የአዲስ ታይምስ መፅሔቶች ባለቤትና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ከታሠረ ትናንት ረቡዕ፤ ጥቅምት 3/2008 ዓ.ም አንድ ዓመቱን ደፍኗል፡፡

የተመስገን ጤና አሳሳቢ መሆኑን ቤተሰቡ ገልጿል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ግን ተመስገን ሕክምና እያገኘ፣ ጤናማም መሆኑን ይናገራል፡፡

የተመስገን ደሣለኝ ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሣለኝ ተመስገንን ረቡዕ፤ ጥቅምት 3/2008 ዓ.ም ዝዋይ ሄዶ ማየቱን፣ ወንድሙ የግራ ጆሮው ሙሉ በሙሉ እንደማይሰማ፣ ጀርባው ላይ ያለው እብጠት እየባሰበት መሆኑንና በጀርባው መተኛት እንደማይችል ገልጿል፡፡

ተመስገን ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሕክምና እንደማያገኝና ቤተሰቡም ለማሳከም ቢጠይቅም ፍቃድ መነፈጉን፣ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ይዘው ሄደው “በማረሚያ ቤቱ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም” የሚል መልስ ማግኘታቸውን ታሪኩ ለቪኦኤ ገልጿል፡፡

ተመስገን ያዘጋጃቸው ከነበሩት መፅሔቶች በአንዱ ላይ አምደኛ የነበሩት የሕግ ባለሙያ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምም ከጥቂት ወራት በፊት ከፕሮፌሰር መስፍንና ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ሆነው

እዚያው ዝዋይ ድረስ ሄደው እንዳዩትና በወቅቱ የግራ ጆሮው ይደማ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

የተመስገን ደሣለኝ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንንም የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ዝዋይ ሄደው ያዩት መሆናቸውንና በቦታው ርቀት ምክንያት ከዚያ በኋላ በአካል እንዳላገኙት ገልፀው ከቤተሰቦቹ ግን አሁን ያለበትን ሁኔታ እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት፣ መንግሥቱ ባወጣቸው ደንቦችና በዓለምአቀፍ ድንጋጌዎችም መሠረት ማንም እሥረኛ ጤንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መያዝ እንደሚገባው፤ አስፈላጊ በሆነ ጊዜም ሕክምና የማግኘት መብት እንዳለው፤ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ የወኅኒ ቤቱ ሃኪም ታራሚው ሕክምና ማናኘቱን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የማረሚያ ቤቱ የፅሕፈት ቤት ኃላፊ ተመስገን አዲስ አበባ ድረስ ተወስዶ ሕክምና ማግኘቱን፤ በማረሚያ ቤቱ ውስጥም እየታከመ መሆኑን፣ ጤናማና እየተንቀሣቀሰ ያለ መሆኑን ገልፀው ጤንነቱ ታውኳል፤ ሕክምና ማግኘት አልቻለም የተባለው ሃሰት መሆኑን ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ተናግረዋል፡፡

ጠበቃው አቶ አምሃ ግን አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ አለመታከሙን፣ ሄዶ ቢሆን ኖሮ እርሣቸው ያውቁ እንደነበር ተናግረዋ የማረሚያ ቤቱን የሥራ ኃላፊ መግለጫ አስተባብለዋል፡፡

ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG