በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ኢትዮጵያ ድርቅ ተከሰተ፤ በአገሪቱ የኑሮ ውድነት በዚህ ወር በ25 ከመቶ አሻቀበ


ባሳለፍንው የመጋቢት ወር የሸቀጦች ዋጋ በ25ከመቶ መጨመሩን የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል። ይሄም በየካቲት ወር ከነበረው የ16.5 ከመቶ የዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ፤ የዋጋ ነረት አስከትሏል።

በየወሩ ኤጀንሲው የሚያወጣው ሪፖርት ከወር ወር የሚተላለፈው የ12 ወር የዋጋ መወደድን የሚያሳየው አማካይ አሃዝ ወደ 11.3 ከመቶ አድጓል።

በመጋቢት ወር በምግብ ዋጋ ላይ የታየው የዋጋ ውድነት 5.8 ከመቶ ነው። የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ያሲን ሙሳ በመጋቢት ወር ላይ የታየው የዋጋ ንረት ከጥቅምት2001 ዓ.ም ወዲህ ያልታየ ጭማሪ መሆኑን ይናገራሉ።

የሸቀጦች ዋጋ ንረቱ የተከሰተው፤ መንግስት በጥር ወር የዋጋ ተመን አውጥቶ ገበያውን ለማረጋጋት መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። በሰሜን አፍሪካ የምግብ ዋጋ ጭማሪ ለዘመናት የቆዩ አስተዳደሮችን ከገረሰሰ ወዲህ ኢትዮጵያን ለ20 አመታት ያስተዳደረው ኢህአዴግ የሸቀጦችን ዋጋ በተመን አግዶ ነበር።

ሆኖም አልተሳካም። የዋጋ ጭማሪው በገበያው ላይ እጥረት በመፍጠሩ በተጓዳኝ የጥቁር ገበያ ውስጥ ውስጡን ሸመታው ጦፎ ነበር የሰነበተው። በዚህ ምክንያት መንግስት በቀጥታ ስኳርና ዘይት የመሳሰሉ አላቂ እቃዎችን ማከፋፈል የጀመረበት ሁኔታ ይስተዋላል።

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚተነብዩት የሀገሪቱ የዋጋ ውድነት በሚያዝያ ወርም ይቀጥላል። በተለይ ከጥቂት ቀናት በፊት የነዳጅ ዋጋ በ14 ከመቶ እንዲጨምር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ፤ ትንበያው እውን እንደሚሆን ባለሙያዎቹ አይጠራጠሩም።

በሌላ በኩል ደግሞ የአደጋ መከላከልና የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅቱ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጨምሯል ሲል በዚህ ሳምንት አስታውቋል።

የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ በጥር ወር መጀመሪያ 2.8 ሚሊዮን ዜጎች የውጭ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቆ፤ ተገቢው እርዳታም እንዲደረግለት ለጋሾችን ጠይቆ ነበር። ለቪኦኤ በስልክ ቃላቸውን የሰጡት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ታደሰ በቀለ፤ የተረጂዎቹ ቁጥር 3.2 ሚሊዮን እንደሆነ ገልጸዋል።

“ለደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ ማስተባበር ስራን በማዘጋጀት ላይ ነን። ባስቀመጥናቸው መስፈርቶች መሰረት አጋሮቻችን አብረውን እንዲሰሩም እንፈልጋለን። ይሄም የከብት ቀለብ ማቅረብ፤ የህጻናት ምግብና የመሳሰሉት ናቸው። በነዚህ ላይ አጋዦቻችን እንዲረባረቡ ጥሪ እናቀርባለን።”

የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) አርብለት ባወጣው መረጃ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ሳቢያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል። በዚህ ሳቢያ የግጦሽ መሬት ሲመናመን አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ስፍራ ወደ ግጭት ያመራሉ የሚል ስጋት አለው WFP.

በአዲስ አበባ የWFፒ ቃል-አቀባይ ሱዛና ኒኮል ውሃና የከብት መኖ ለማጓጓዝ ጥረት ቢደረግም፤ ከችግሩ ስፋት አንጻር፤ ሁሉን ለማዳረስ አለመቻሉንና የከብቶች ሞት መቀጠሉን ይናገራሉ።

“የከብት መኖና የውሃ እጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች በእጅጉ የጠና ሆኗል። ከብቶቹ መሞታቸው ከቀጠለ፤ ችግሩ ይባባስና የሁሉንም ሰው ደጅ ያንኳጓል። ሰዎች እራሳቸውን መመገብ ሊቃቅታቸው ይችላል፤ ኑሯቸውም ይቃወሳል። “

የኢትዮጵያ የምግብ እጥረት የተከሰተው ባለፈው ሳምንት የአለም ባንክ በአለም ዙሪያ የ36 ከመቶ የምግብ ዋጋ ጭማሪ በዚህ አመት እንደተስተዋለ ይፋ ባደረገበት ማግስት ነው።

የአለም ባንክ ፕሬዝደንት ሮበርት ዞለክ በጉዳዩ “በቋፍ ላይ እንገኛለን” ሲሉ አሳሳቢነቱን በአጽንዖት ገልጸዋል።

ዩናይትድ ስቴይትስ ለኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ከሚሰጡ አገሮች ግምባር ቀደሟ ናት። የአለም የምግብ ድርጅት ባጠናቀረው መረጃ መሰረት ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ዩናይትድ ስቴይትስ 58 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የምግብ እርዳታ ለኢትዮጵያ ሰጥታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለየኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በመብራት ፍጆታ ዋጋ ላይ እስከ 200% ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ማጠናቀቁንና ይህንንም ጥናት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተልኮ እንደነበረና፤ ለክለሳ ተመልሶ ወደ መብራት ሃይል መላኩን ሳምንታዊው የንግድና ኢኮኖሚ ጋዜጣ ካፒታል ዘግቧል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG