በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጲያ የርቀት ትምህርት ተከለከለ


የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህግና መምህራን ስልጠና ትምህርት እንዳይሰጡ ታገደዋል

የሁለት ሺህ ሶስት አዲስ የትምህርት ዓመት በተቃረበበት ባሁኑ ሰዓት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚመለከተው መመሪያ መነጋጋሪ ሆኗል። የውሳኔው ተቃሚዎች ርምጃው የተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ሲናገሩ መንግሥት ከቁጥር ይልቅ ለጥራት ቅድሚያ ለመስጠት ተብሎ ነው ብሏል ።

ሁለት ሳምንት ከቀሩት አዲስ ዓመት ጀምሮ የመንግሥትም ሆኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለርቀት ትምህርት መመዝገብ አይችሉም ። ቀደም ሲል የመዘገቡዋቸውን ግን ማስጨረስ ይችላሉ።

አዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ የግሎቹን ብቻ በተመለከተ ባሰፈረው ደምብ የህግና የመምህራን ትምህርት ስልጠና ማስተማር አይፈቀድላቸውም።

ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዚደንት አቶ የወንድወሰን ታምራት “በግሉ ተቋማት የጥራት ችግር ያለባቸው እንንዳሉ አይካድም፤ የሚያሳዝነው የዘርፍ ችግር ተደርጎ መወሰዱ ነው” ብለዋል።

ካሁን ቀደም መንግሥት ራሱ ባቋቋመው የጥራትና አግባብነት ኤጄንሲ ዘጠኝ የመንግሥትና አምስት የግል ዩኒቨርስቲዎች ጀረጃ ተለክቶ አዳዲሶቹ የግል ተቋማት ጥሩ ስራ እየሰሩ እንዳሉ ባንዳንድ ቦታ ደግሞ በጣም ነባርና ግዙፍ የመንግሥት ተቋማት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች እንደሆኑ ታይቷል በማለት አቶ የወንድወሰን አስታውሰዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የውጭ እና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ አባተ የርቀት ትምህርት የተከለከለው በሁሉም ተቋማት ደረጃ መሆኑን ገልጠው የህግና የመምህራን ስልጠናው ለምን የግሉን ብቻ ተመለከተ ለተባሉት መንግሥት ራሱ ባዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት መምሪያ ጥቅል ቀዳሚ ቦታ የተሰጠው የመምህራንን ጥራት ማስጠበቅ በመሆኑ በዚያ መሰረት እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የህግ ትምህርቱን በተመለከተ በየቦታው ስራ የሌላቸው የህግ አዋቂዎች እየተፈጠሩ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ስራ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ የገበያ ፍላጎቱ ተጠንቶ መከናወን ስላለበት እንደየሁኔታው መንግስት እንዲቆጣጠረው ስለተፈለገ ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበር ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ተሰብስቦ እየመከረ ነው።

XS
SM
MD
LG