በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መለስ ዜናዊ በሌሉበት የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ተጀመረ


የአስተናጋጇ ሃገር መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ያልተለመደ” በተባለ ሁኔታ ያልተገኙበት 19ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሯል፡፡

(ይህ ገፅ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ኮምፕዩተርዎ ከአንድ በላይ ድምፅ ማጫወቻ አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ፅሁፍ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸው፡፡)

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመክፈው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብለው ተጠብቀው የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ በመክፈቻው ላይ የተወከለችው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ነው፡፡

ከእርሣቸው ጋር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሣደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ ተገኝተዋል፡፡

ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት - ኔፓድ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሊቀመንበርነት የሚመራ ሲሆን ትብብሩ ትናንት ባደረገው ስብሰባ ላይም አልተገኙም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ ስብሰባዎች ላይ ያልተገኙበት ምክንያት ለጊዜው ከመንግሥትም ይሁን ከአፍሪካ ሕብረት ለጊዜው የተገለፀ ነገር የለም፡፡

የሕብረቱ ጉባዔ በመክፈቻው ላይ በአካባቢው ላሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ የሚያደርግ መልዕክት ተሰምቶበታል፡፡

በጉባዔው ላይ የተናገሩት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዣን ፒንግ አፍሪካ የራሷን ችግሮች እራሷ እንድትፈታ አሳስበዋል፡፡

ጉባዔው በንግድና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚነጋገር ታውቋል፡፡

ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ያሉ የታጠቁ አማፂያንን ለመውጋት ሠራዊት ሊልክ እንደሚችል የአፍሪካ ሕብረት ማስታወቁና በሰሜን ማሊም የሚንቀሣቀሱ የታጠቁ የሙስሊም አማፂያንን ለመፋለም የተነደፈውን ዕቅድም እንደሚደግፈው አመልክቷል፡፡

ጉባዔው በተጨማሪም እልባት ሳይሰጠው በእንጥልጥል ያለውን የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበር የመምረጥ ሥራም ከአሁኑ ጉባዔ ሥራዎች አንዱ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

ለቦታው ከዣን ፒንግ ጋር የሚወዳደሩት የደቡብ አፍሪካዋ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ንኮሣዛና ድላማኒ-ዙማ ናቸው፡፡

ባለፈው ጥር በተካሄደው ምርጫ ሁለቱም ተፎካካሪዎች ሥራውን ለማሸነፍ የሚጠበቅባቸውን ከሕብረቱ አባላት የሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምፅ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከማጫወቻዎቹ አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸውና የሚጫወተውን እንደገና ያስጀምሩት፡፡ )


XS
SM
MD
LG