በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለጥያቄዎ መልስ፤ “ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በሊብያ”


ከሣምንታት በፊት በሊብያ መንግሥት ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሣ ወዲህ በሃገሪቱ የሚኖሩ ስደተኞች በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ጥቁር አፍሪካዊያን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡

በሕዝባዊው አመፅ መጀመሪያ አካባቢ አልጃዚራ ቴሌቪዥን “የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያላቸው” ያላቸውን ቅጥረኛ ወታደሮች ገልፆ ከዘገበ ወዲህ ተቃዋሚው ሕዝብ በአጠቃላይ ጥቁር አፍሪካዊያንን “ዐይናችሁ ላፈር” ብሏል፡፡ ሁሉም ሊብያዊያን ማለት ባይቻልም አብዛኞቹ “ባዕዳን ውጡልን” እያሉ ነው በማለት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ስደተኞች ሰሞኑን የሮሮ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡

እንደትሪፖሊ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የሚኖሩ ስደተኞቹ በሮቻቸውን ዘግተው በፍርሃት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምግብ እያለቀባቸው ነው፤ ወደውጭ ከወጡ ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ እንደቤንጋዚ ካሉ ከተሞች ደግሞ “ውጡ” ተብለው ወደ ወደቡ ተባርረዋል፤ እዚያ እየተንገላቱ ነው፡፡

ከዚያም በላይ በግርግሩ ውስጥ የተደፈሩ ሴቶች እንዳሉ፤ ሕይወታቸውንም ያጡ በርካታ እንደሆኑ ስደተኞቹ ይናገራሉ፡፡ ቁጥራቸው አይታወቅም፡፡ በጥይትና በሥለት የቆሰሉ ሕክምና ተነፍጓቸዋል፡፡ ቤተሰብ፣ ጓደኛ ተለያይቶ ማን የት እንደደረሰ አይታወቅም፡፡

ምን ይበጃል? ከዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ፣ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን ምን ይጠበቃል? መላ እንዲጠቁሙን እንግዶች ጋብዘናል፡፡

አባ ሙሴ ዘርዓይ በጣልያን ሃገር “ኤጀንሲያ ሃበሻ” የተባለ ድርጅት መሥርተው ስደተኞችን ሲደረዱ የቆዩና አሁን ሊብያ ውስጥ ቀውስ ሲከሰትም ለመታደግ ፈጥነው የደረሱ ናቸው፡፡ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚኖሩና ለስደተኞች መብት መከበር ብዙ የፃፉና የሚሟገቱ ናቸው፡፡

በአሜሪካ ድምፅ “ለጥያቄዎ መልስ” ተጋብዘዋል፡፡

ለዝርዝርና ተጨማሪ መረጃ ውይይቱን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG