በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቢቢሲ፣ ባንድ ኤድና የኢትዮጵያ መንግሥት


በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር በ1984 እና 85 በረሃብ ለተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የተለገሠ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት እርዳታ በያኔው ሸማቂ ድርጅት ህወሓት ለመሣሪያ ግዢ ውሏል በሚለው የቢቢሲ ዘገባ ዙሪያ ውዝግብ ቀጥሏል።

ቢቢሲ ባለፈው መጋቢት ወር ባወጣው በዚህ ዘገባ ላይ የእርዳታ ገንዘቡን ያሰባሰበውን የሙዚቃ ቡድን "ባንድ ኤድ"ን የመራውን ሙዚቀኛ ሰር ባብ ጌልዶፍን ከትናንት በስቲያ ባሠራጨው ዘገባ ይቅርታ መጠየቁን ከዚህ በቀደመው ዘገባ አስደምጠናል።

ከኢትዮጵያ መንግሥት የኮሚኒኬሽን መሥሪያ ቤት የወጣ መግለጫ ደግሞ "ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግሥትም ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው" ይላል፡፡ ባንድ ኤድን እና ሰር ባብ ጌልዶፍን የቅርታ የጠየቀበትን ምክንያት እንዲሁም ለኢትዮጵያ መሪዎች የ"ይቅርታ ይገባናል" መግለጫ ከቢቢሲ መልስ ጠይቀናል፡፡ ከቢቢሲ ዋና ማዕከል የዓለምአቀፍ ኮሚኒኬሽንስ አባል ፒተር ኮነርስ ዓለምአቀፉ የዜና ማሠራጫ ድርጅት ቢቢሲ በዌብ ሣይቱ ላይ ያወጣውን መግለጫ አንብበዉልናል።

«ፕሮግራሙ ባንድ ኤድ ለዕርዳታ የሠጠው ገንዘብ ለሌላ መዋሉን የሚያረጋግጥ ውንጀላ አያቀርብም። ይሁንና ይህን ዓይነት ግንዛቤ በፕሮግራሙ ሳቢያ ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ያምናል። በተጨማሪም ከርዕሱ ጋር በተዛመደ ያቀረብናቸው አንዳንድ ዘገባዎችም ይህንኑ ግንዛቤ እንዳጠናክሩ እንረዳለን።

በመሆኑም የተባለው ውንጀላ በተለይ ከባንድ ኤድ ጋር የተያያዘ ያለመሆኑን በግልፅ ማሣየት እንደነበረበት ቢቢሲ ስህተቱን ያምናል፤ ይቅርታም ይጠይቃል።» ይላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽንስ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትናንቱ መግለጫው "ቢቢሲ ባብ ጌልዶፍን ይቅርታ ጠይቆ እኛን ቸል ማለቱ እንግዳ ነው" በማለት ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግሥት ስማቸው ሰለጎደፈ ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው ብሏል። በፒተር ኮነርስ የተነበበው መግለጫ የሚከተለውን መልስ ሰጥቶአል።

«ውሳኔው ፕሮግራሙ በተከተለው የጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ያለውን አመኔታ የሚያረጋግጥ ነው። ህወሓት ለረሃብ ዕርዳታ የታሰበውን ገንዘብ ለሌላ እንዳዋለውና ከዚህም ውስጥ የተወሰነው ለጦር መሣሪያ መግዣ መዋሉን የሚያረጋግጡ በርካታ ምንጮች ነበሩ።»

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንት ዝግጅታችን የህወሃት ታጋይና የፋይናንስ ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ገብረ መድህን አርአያ ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ የህወሓት መሪዎች ከዓለምአቀፍ ለጋሾች ለድርቅ ረሃብተኞች በእርዳታ የተላከ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብና እህል ለድርጅታቸው መሣሪያ መግዣና ለሌሎች ጉዳዮች ማዋላቸውን አውቃለሁ ማለታቸውን ዘግበናል። ሆኖም ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ ዶክተር አረጋዊ በርኸ "የለጋሾት እርዳታ ለመሣሪያ ግዢ አልዋለም" ብለዋል የሚል ዘገባ ማስተላለፋችን ስህተት ነው፡፡ ስለ ስህተቱ ይቅርታ እንጠይቃለን። በዚያ ዙሪያ ብዙ አድማጮች መልዕክት ልካችሁልናል፤ ስህተቱን በመጠቆማችሁ እናመሰግናል፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር ይህ የቢቢስ ዜና ይፋ እንደሆነ ባልደረባችን አዲሱ አበበ ከዶክተር አረጋዊ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ደግመን እናሰማለን።

የትላንቱን ዘገባችንን የተከታተሉ የቀድሞ የህዋሓት ታጋይ ነኝ ያሉ አቶ አማረ የሚባሉ አድማጭ "በ1984 እና 1985 ዓ.ም. ለድርቅ ተጎጂዎች ካለም የጎረፈውን እርዳታ ህወሓት ለሌላ ጉዳዮች እንዳዋለ እኔም አውቃለሁ፤ አቶ ገብረ መድህን አርአያ ብቻ አይደለም" ሲሉ ለትግርኛ ክፍል ባልደረባችን ተወልደ ተስፋጋብር በስልክ ገልፀዋል። እህሉን ማን እንደሸጠ ለማንስ እንደተሸጠና አቶ አማረ ምን ማስረጃ እንዳላቸው ጠይቀናል።

"ህወሓት ከደርግ የማረካቸው መኪኖች ሊሆኑ አይችሉም?" ወይ ሲል ተወልደ ላቀርበው ጥያቄም "አይደለም" ብለዋል አቶ አማረ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ጉዳይ በሚመለከት አሁን ያሉት የህወሓት መሪዎች ከለጋሹ ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ያገኙትን እርዳታ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ህይወቶችን ለማዳን እንደተጠቀሙበት ካሁን ቀደም መናገራቸው ይታወሣል። የተለገሰው ገንዘብም ለድርጅቱ መሣሪያና ቁሣቁስ መግዣ መዋሉንም አስተባብሏል። (ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ)

XS
SM
MD
LG