በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ሕብረት መፍትሔ ለአይቮሪ ኮስትና ለሊብያ


የአይቮሪ ኮስት ያለፈው ምርጫ አሸናፊ አላሣን ዋታራ ናቸው ሲል የአፍሪካ ኅብረት በማያሻማ ሁኔታ ወስኗል፡፡ የሃገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት የአዲሱን ፕሬዚዳንት ቃለ መሃላ እንዲያስፈፅም አዝዟል፡፡

አላሣን ዋታራ ትናንት ግዙፍ ድል ነው የጨበጡት፡፡ "የአይቮሪ ኮስት ፕሬዚዳንት እንግዲህ እኔ ነኝ፤" እያሉ በብርቱ ሲሟገቱ ሰንብተዋል፡፡ ይህንን ለማስጨበጥም አዲስ አበባ ድረስ ሄደው የአሕጉራዊው ኅብረት የወደፊት አቻዎቻቸውም "አዎ ከእንግዲህ የአይቮሪ ኮስት ርዕሰ ብሔር እርስዎ ነዎት" ሲሉ በግልፅ አፅድቀውላቸዋል፡፡ እንግዲህ የሚቀራቸው ቃለ መሃላቸውን ጨርሰው ወደ ያማሱክሮ ቤተ መንግሥት መዝለቅ ነው፡፡

መጭውን ፕሬዚዳንት አላሣን ዋታራን ከምርጫው ወዲህ የነበረውን አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ሆቴል ውስጥ ተከብበው ካሣለፉባት ከንግድ መናኸሪያዋ አቢዦን ይዟቸው ወደአዲስ አበባው ጉባዔ የበረረው አይሮፕላን ተመልሶ የኮት ዲቯርን አየር እንዳይዘልቅ ባግቦ ቢከለክሉም የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ይህንን የበረራ እገዳ ረግጦ ነባር እንቅስቃሴዎቹን እንደሚቀጥል ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን ትናንትናውኑ አስታውቀዋል፡፡

"የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮውንና ንብረቶቹን ለመከላከል፣ በተለይ ደግሞ ሲቪሎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ ይወስዳል" ሲሉ ሚስተር ባን አስጠንቅቀዋል፡፡

ሕገመንግሥታዊው ፍርድ ቤት ሣይውል ሣያድር ዋታራን ቃለ መሃላ እንዲያስፈፅም የአፍሪካ ሕብረት ከወሰነ በኋላ አላሣን ዋታራ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃል ስለ ስብሰባው አጠቃላይ አካሄድ ተናግረዋል፡፡

"ከርዕሣነ-ብሔር ቡድኑ ጋር ጥሩ ስብሰባ ነው ያደረግነው፡፡ በአይቮሪ ኮስት ሕዝብ የተመረጥኩት ፕሬዚዳንት እኔ መሆኔን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ ይህ የመጨረሻ ውሣኔ ነው፤ ከዚህ ወደኋላ ማፈግፈግ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡" ብለዋል ዋታራ፡፡ በተጨማሪም የእርቅ ማዕቀፍ ማሠናዳት፤ ሌሎች ፓርቲዎችንና ሲቪል ማኅበረሰቡንም ግምት ውስጥ ያስገባ መንግሥት መመሥረት፣ ሚስተር ሎሮን ባግቦ በክብር ሊሰናበቱ የሚችሉበትን ሁኔታ ሊያመቻቹ ይችሉ እንደሆነ መሪዎቹ የጠየቋቸው መሆኑን ሚስተር ዋታራ አመልክተዋል፡፡

በኅዳር 19ኙ ምርጫ መሸነፋቸው በግልፅና በተለያዩ አካላት ተደጋግሞ የተረጋገጠባቸው ሚስተር ባግቦ በአዲስ አበባው ስብሰባ ላይ ባይገኙም ተወካዮቻቸው ግን የመሪዎቹን ውሣኔ "ፍፁም ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ፈጥነው ተቃውመዋል፡፡

አጠቃላዩን ሂደት በብርቱ ሲቃወሙና ሽማግሎችንም አሻፈረኝ እያሉ ሲያባርሩ የሰነበቱት ባግቦ አዲሱን የአፍሪካ ኅብረትን ውሣኔ እንዴት እንደሚያስተናግዱና ለትዕዛዙም እንደሚገዙ ግልፅ ገና ግልፅ ባይሆንም የኅብረቱ የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽነር ራምታኔ ላማምራ ግን "ተሰናባቹ እንዲወጡ ተነግሯቸዋል፤ የቡድኑ ውሣኔ የፀናና ተፈፃሚ ይሆናል" ብለዋል፡፡

"እምቢታን መልስ ነው ብለን አንቀበልም፡፡ ፅናት ያለን ሰዎች ነን፤ አቋማችንን ይዘን በብርታት እንገፋለን፤ የኮት ዲ ቯር ባለጉዳዮችም ሃገራቸውን መልሰው ወደ እርስ በርስ ብጥብጥ ለመክተት አቅምና ዝግጁነት ይኖራቸዋል ብለን አናምንም፡፡ የአሁኑ ታሪካዊ ዕድል እንዲያመልጥም የሚፈቅድ ኃላፊነት የሚሰማው መሪ ይኖራል ብዬ ከቶ አላስብም፡፡" - የራምታኔ ላማምራ ቃል ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ባሣለፈው ለአላሣን ዋታራ ዕውቅና የመስጠት ውሣኔ ምክንያት የፖለቲካው ቀውስ እንግዲህ ይበልጥ እንደሚበላሽ ግን የባግቦ መንግሥት ያስጠነቀቀው ፈጥኖ ነው፡፡

በሌላ በኩል የባግቦ መንግሥት የኮኮ ምርት ኢንደስትሪውን ለመውረስ መወሰኑ ሌብነት ነው ሲሉ ተተኪው የአይቮሪ ኮስት ፕሬዚዳንት አላሣን ዋታራ ገልፀዋል፡፡

ሃገራቸው ከተዘፈቀችበት የምጣኔ ኃብት ዝቅጠት ፈጥና እንድታገግምም እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ትምህርታቸውን በአሜሪካ የተከታተሉት የምጣኔ ኃብት ባለሙያ፣ ቀድሞ የዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት አላሣን ዋታራ እንደ ፕሬዚዳንት የሚገጥማቸው ከባዱ ፈተና ሃገራቸውን ከእርስበርስ ብጥብጥ ለማዳን ይችሉ ዘንድ የተፈጠረው ቁስል እንዲያሽር መሥራቱ መሆኑን አመልክተው የሃገራቸውን የገንዘብና የምጣኔ ኃብት ጤንነት ለማከም ግን ልምድና ዕውቀታቸው ብዙ እንደሚያግዛቸው በመተማማን ስሜት ተናግረዋል፡፡

"ወገኖቼ ቀደም ሲል ምን እንደሠራሁ ያውቃሉ፡፡ - አሉ ዋታራ ስለ ዜጎቻቸው ሲናገሩ - የአይኤምኤፍ ምክትል ዳይሬክተር ሆኜ በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችና በሌላውም ዓለም ምን እንደሠራሁ ያውቃሉ፡፡ ለኮት ዲ ቯርም ግዙፍ ዕቅዶች አሉኝ፡፡ ኢኮኖሚው በአጭር ዓመታት እንደሚመነደግ እተማመናለሁ፡፡"

ይህ በእንዲህ እንዳለ አምስት አባላት የሚገኙበት የመሪዎች ቡድን ወደ ሊብያ ለመላክ ሕብረቱ በተናጠል ወስኗል፡፡ ቡድኑ በአማፂያኑና በፕሬዚዳንት ሞማር ጋዳፊ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ እንዲቆም ያሸማግላል፡፡

ምንም እንኳ ኮሎኔል ጋዳፊ በስብሰባው ላይ ባይገኙም ሰዎቻቸው ግን ወደ ምርጫ ሊወስዱ የሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በዝግ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ቃል መግባታቸውን ኮሚሽነር ላማምራ ገልፀዋል፡፡

ሃገራቸው ለፖለቲካ ለውጦች በቁርጠኝነት መቆሟን የሊብያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያስታወቋቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሊብያ ላይ ማዕቀቦችን የመጣልና ለበረራ የተከለከለ ቀጣና የመደንገግን ሃሣብ መሪዎቹ ተቃውመዋል፡፡

የመሪዎቹ ቡድን ፈጥኖ ተኩስ አቁም በሚደረስበት ሁኔታ ላይ እንደሚሠራ የጠቆሙት ላማምራ የሽምግልና ቡድኑ አባል የሚሆኑት የመንግሥታት መሪዎች በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ እንደሚሰየሙና ሥራቸውን ለመጀመርም ወዲያው ወደ ሊብያ እንደሚጓዙ አስታውቀዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG