በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ ከ15 ዓመታት በፊት በዘፈቀደ ያሰረቻቸውን እንድትፈታ አምነስቲ አሳሰበ


ከ15 ዓመታት በፊት ከሕግ ውጭ ተይዘው እሥር ላይ ያሉት የፖለቲካ ሰዎችና ጋዜጠኞች ሁሉ በአፋጣኝና ያለ ቅድመ-ሁኔታ እንዲለቀቁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ዓለምአቀፍ ቡድን ይህንን ጥሪ ያሰማው ሁሉም እሥረኞች በሕይወት መኖራቸውን የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጡ መልካም ዜና መሆኑን ባሳወቀበት መግለጫው ነው፡፡

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳልሕ ከራዲዮ ፍራንስ አንተርናሲዮናል - አርኤፍአይ ጋር ባደረጉትና ትናንት፤ ሰኞ በተላለፈ ቃለ-ምልልስ እሥረኞቹን “የፖለቲካ እሥረኞች” እያሉ መጥራታቸውንና “ሁሉም በሕይወት ያሉ” መሆናቸውን ተናግረው “መንግሥት ሲወስን ለፍርድ እንደሚቀርቡ” ማመልከታቸውን አምነስቲ አመልክቷል፡፡

በመስከረም 1993 ዓ.ም ተይዘው ከታሠሩት መካከል አሥራ አንድ ፖለቲከኞችና አሥር ጋዜጠኞች እንደሚገኙ አምነስቲ ጠቁሞ የኤርትራ ባለሥልጣናት እሥረኞቹ ስላሉበት ቦታም ሆነ ስለጤናቸው ሁኔታ እስከአሁን ለቤተሰቦቻቸው ከመግለፅ አሻፈረኝ ብለው መቆየታቸውን ገልጿል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሕሊና እሥረኞች እንደሆኑ የሚያምነው ሃያ አንዱ ሰዎች እንዲለቀቁ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ሲሟገት መቆየቱን ያስታወሱት የቡድኑ የምሥራቅ አፍሪካ፣ የቀንዱና የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን “እሥረኞቹ ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው እንዲህ ለተራዘመ ጊዜ ያለ ክሥና ያለ ፍርድ መቆየታቸው የፍትህ መጥፋትን ያሳያል” ብለዋል፡፡

“ቀድሞም ቢሆን መታሠር እንዳልነበረባቸው ሁሉ አሁንም ያለአንዳች ቅድመ-ሁኔታ መለቀቅ አለባቸው” ብለዋል ጃክሰን አክለው፡፡

አሥራ አንዱ የገዥው የዴሞክራሲና የፍትሕ ሕዝባዊ ግንባር - ሕግዴፍ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት የተያዙት በሃገሪቱ ለውጥና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ የሚጠይቅ ግልፅ ደብዳቤ በመስከረም 1993 ለመንግሥታቸውና ለፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ከፃፉ በኋላ ሲሆን ጋዜጠኞቹ በተከታዩ ሣምንት ውስጥ መታሠራቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚሁ ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

ከ15 ዓመታት በፊት ከሕግ ውጭ ያስረቻቸውን ሁሉ ኤርትራ እንድትፈታ አምንስቲ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:18 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG