በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለስድስት ሳምንታት በሶማሊ ክልል ታግተው የነበሩት የWFP ሰራተኞች ተለቀቁ


ከአዲስ አበባ 650 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው የዳናን ከተማ ልጇን አቅፋ፤ በኦጋዴን ክልል በቀን 8 ህጻናት ከረሃብ ጋር በተያያዘ ይሞታሉ
ከአዲስ አበባ 650 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው የዳናን ከተማ ልጇን አቅፋ፤ በኦጋዴን ክልል በቀን 8 ህጻናት ከረሃብ ጋር በተያያዘ ይሞታሉ

በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሰኞለት ሁለቱን ሰራተኞች ለWFP ማስረከቡን ያስረከበው ሰኞለት ነበር። የአለም የምግብ ድርጅት በዛሬውለት ሁለቱ ታጋቾች በአዲስ አበባ ከቤተሰባቸው ጋር መቀላቀላቸውን ይፋ አድርጓል።

ከስድስት ሳምንታት በፊት በሶማሊ ክልል አንድ የአለም የምግብ ድርጅት WFP ሰራተኛ ተገድሎ ሁለቱ የደረሱበት መጥፋቱ ይታወሳል።

በክስተቱ ላይ የተለያዩ መረጃዎች ይፋ ሲሆኑ፤ የአለም የምግብ ድርጅት ሰራተኞቹ ላይ አደጋ መድረሱንና፤ የተሰወሩትን ፈልጎ ለማግኘት ተማጽኖውንና ጥረቱን ማጠናከሩን ሲገልጽ ቆይቷል።

በዛሬውለት የአለም የምግብ ድርጅት በኦጋዴን ተሰውረው የቆዩት ሁለቱ ሰራተኞቹ መለቀቃቸውን አረጋግጧል።

“በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ያገለግሉ የነበሩ ባልደረቦቻችን በሶማሊያ ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ተለቀዋል” ሲሉ የWFP ቃል አቀባይ ፋራሃን ሃክ ተናግረዋል።

“አሁን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ይገኛሉ። ጤንነታቸውን ለማረጋገጥ የህክምና ምርመራና፤ የመንፈስ መረበሽ የስነ-ልቦና ምክር እየተሰጣቸው ነው።”

ታጋቾቹ በመልካም ጤንነት ላይ ቢገኙም፤ የህክምና ማረጋገጫ ለማግኘት ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።

እነዚህ የእርዳታ ሰራተኞችን ማን እንዳገታቸው የአለም የምግብ ድርጅት የሰጠው መግለጫ የለም። ከዚህ በቀደሙ ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሰራተኞቹ ላይ ጥቃት አድርሶ ሁለቱን ማገቱን ገልጾ ነበር።

ኦብነግ በበኩሉ የWFP ሰራተኞች የታገቱት በኢትዮጵያ ሰራዊት ነው ሲል አስታውቋል። በሶስት ሳምንታት በፊት በገላልሼ ከተማ በተደረገ ውጊያ ኦብነግ እነዚህን ታጋቾች ከኢትዮጵያ ሰራዊት ማስለቀቁን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል።

ቪኦኤ ያነጋገራቸው የአካባቢው ሰዎች በ WFP ሰራተኞች ላይ ጥቃቱን ያደረሱት የኦብነግ ታጣቂዎች እንደሆኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ለመሆኑ የ WFP ሰራተኞች ከተለቀቁ በኋላ ስለ-አጋቾቻቸው ምን መግለጫ ሰጡ?

እንዲህ ያለ ክስተት ካለፈ በኋላ የታገቱትን ሰዎች ማነጋገር የተለመደ አሰራራችን ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ፋራሃን ካን፤ “ባለፉት ስድስት ሳምንታት የደረሰባቸውን ሁሉ በዝርዝር ይነግሩናል። ይሄንን ማጣራት ካደረግን በኋላ የደረሰባቸውን ሁሉ መረዳት እንችላለን። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ መስጠት አንችልም” ብለዋል።

በሌላ በኩል በአለማችን በ70 አገሮች ወደ 90 ሚሊዮን የሚሆኑ የተራቡ ሰዎችን የሚመግበው WFP በአፍሪካ ቀንድ ላለፉት ስልሳ አመታት ታይቶ የማያውቅ ድርቅ መከሰቱን ገልጿል።

አስር ሚሊዮን ዜጎች የከፋ የምግብ እጥረት ለረሃብ እንዳጋለጣቸው ድርጅቱ በትናንትናውለት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸው WFP በኬንያ 3.5 ሚሊዮን፣ በሶማሊያ 2.5 ሚሊዮን፣ በሰሜን ምስራቅ ዩጋንዳ 600ሽህ፣ እና በጂቡቲ 120 ሽህ ሰዎች መራባቸውን አሳስቧል።

“ዋናው የችግሩ መንስዔ ድርቅ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት በስልሳ አመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ነው የተከሰተው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እዲሉ፤ የምግብ ዋጋ መናርም ለችግሩ ተጠቃሽ ነው። ስለዚህ አስቸኳይ እርዳታ ለማከፋፈል የሚያስችለን የገንዘብ እርዳታ እንዲሰጠን በመጠየቅ ላይ ነን” ብለዋል ፋራሃን ካን።

በችግር ላይ ከወደቁት 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች WFP ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉትን በእጅጉ የተጠቁ እርዳታ ለመስጠት አቅዷል። ሆኖም የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ እንደሚሉት ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም WFP የለውም።

ይህንን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ፤ የሚበሉት ለሌላቸው ህጻናት አልሚ ምግብ ለማቅረብ፤ ለእናቶች የህክምናና የምግብ አቅርቦት ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል ። በዚህ ላይ የአካባቢው መንግስታትም ሃላፊነት እንዳለባቸው የWFP ቃል አቀባይ ፋራሃን ሃክ ያስገነዝባሉ።

“አንዱ የምንጠይቃቸው ነገር፣ በአካባቢው የሚታየውን ሁኔታ ለመታደግ የቀረበውን የሰብዓዊ እርዳታ ጥሪ ክብደት ሰጥተው፤ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ነው። መንግስታት ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎቻቸው እርዳታ ማቅረብ ይገባቸዋል።”

በዚህ ድርቅ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ህጻናት መሆናቸውን የገለጸው የአለም የምግብ ድርጅት፤ ቀዳሚ ተጠቂዎቹን ለመታደግ የእርዳታ ጥሪው አስቸኳይ መሆኑን አስምሮበታል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG