በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች አካላት የሚደርስበት ጫና እንደሌለ ገልጸ


"በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የይዘት ቅድመ-ምርመራ የለም” ስቲቭ ሬዲሽ

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዝግጅቶቹን እንዲቀይር ከኢትዮጵያ መንግስት የሚደርስበት ምንም አይነት ጫና እንደሌለ አስታወቀ።

የሚመራው በነጻነት እንዲያገለግል በአዋጅ በተቋቋመበት ህግና በቻርተሩ ሃላፊነት መሆኑን ቪኦኤ ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት በቪኦኤ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል ላይ ያቀረበውን ክስና፣ የቪኦኤ ምላሽ፣ ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ጋር ተጣምረው እንዲህ ተዘግበዋል።

በትናንትናውለት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዋና መስሪያቤት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲስተጋቡ የቆዩ፤ በሬድዮ ጣቢያው የውስጥ አሰራር ዙሪያ ያተኮሩ ዘገባዎች ጡዘት ነበር።

ሰልፈኞቹ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ከኢትዮጵያ መንግስት ጫና እየደረሰበት እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸው፤ ቪኦኤ ለዚህ ጫና እንዳይንበረከክ ጠይቀዋል።

ጊዚያዊው የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስራ አስኪያጅና ዋና አዘጋጅ ስቲቭ ሬዲሽ ቪኦኤ ከኢትዮጵያ መንግስት ዝግጅቶቹን እንዲቀይር ምንም አይነት ጫና እንደማይደርስበት ገልጸዋል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የሚተዳደረው በአዋጅ ነጻ ሆኖ እንዲያገለግል በተቋቋመበት ህጋዊ ማእቀፍና፤ ጋዜጠኞቹና የአስተዳድር አካላቱ በየለቱ በሚያስፈጽሙት ቻርተሩ መሆኑን ሬዲሽ ይናገራሉ።

በዚህም የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ለአድማጮቹ የተሟላ፣ ሚዛናዊና የታመነ መረጃ ሰጭ ዜናዎችን ማሰራጨት ሃላፊነት እንዳለበት ሬዲሽ ይገልጻሉ። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ አቀንቃኝ ታማኝ በየነ፤ በቪኦኤ አሰራር ላይ ስቅታዎች ይታያሉ ይላል።

“ኢትዮጵያውያን በዋሽንግተን ያደረጉትን ስብሰባ ቪኦኤ ለመጀመሪያ ጊዜ አልዘገበም። የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል እንደ ድሮው ሽፋን አላገኘም። እነዚህ ምልክቶች ጤነኛ ሁነው ስላልታዩን ነው። ይህ በአማራጭነት የሚያገለግለው ሜዲያ መዝጋት ህዝብን በጨለማ ውስጥ መክተት ነው ብለን ስለምናምንና ለቪኦኤ ያለንን አክብሮት ለመግለጽ ነው።”

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በኢትዮጵያ የሚሰራበት ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን ያልተመቸ እንደሆነ ጊዚያዊ የቪኦኤ ስራ አስኪያጅ ስቲቭ ሬዲሽ ይናገራሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የመገናኛ ብዙሃን በነጻነት የማይሰሩባቸ አገሮች፤ የአለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዜጎች የሚፈልጓቸውንና ኑሯቸውን በአግባቡ በመረጡት ምልኩ እንዲመሩ የሚያስችሉ የመረጃ አማራጮችን ያቀርባሉ ይላሉ ሬዲሽ።

በዚህም የቪኦኤ ሃላፊነት የዜጎችን ድምጽ ማሰማት፣ ስለ እለት ተለት ኑሯቸው በአንደበታቸው እንዲናገሩ እድል መስጠትን ይጨምራል ይላሉ ሬዲሽ።

ሬዲሽ አክለውም፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስርጭቱን የሚያስተላልፈው በአፍሪካ ቀንድ አማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ለሌላቸው ዜጎች መሆኑን ገልጸው፤ የዜና ሽፋኑም አቢይ አትኩሮቱ በኢትዮጵያ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ድምጽ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ዜጎችም በዚህ የሬድዮ ጣቢያ እንዲናገሩ፣ ሃሳባቸውን በሃገር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ መድረኩን እንደሚሰጥ ሬዲሽ አብራርተዋል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሚመራበት አላማና ሃላፊነት ከየትኛውም አካል ጫና እንዳይደርስበት ተቋማዊና ህጋዊ ነጻነቱ የተረጋገጠ ነው የሚሉት ሬዲሽ፤ ይሄ ጫና በእርግጠኝነት ከኢትዮጵያ መንግስት ሊጣልበት እንደማይችል ይናገራሉ።

ስቲቭ ሬዲሽ በትናንትናውለት ለአፍሪካ ቀንድ ዝግጅት ክፍል፤ ከቪኦኤ የዝግጅት ክፍል መሪ ጆን ሌነን ጋር በመሆን ባደረጉት ስብሰባ ላይ፤ የቪኦኤን ቻርተር በኪሳቸው ሁል ጊዜ እንደሚይዙ አሳይተው፤ ይሄን ቻርተር ጋዜጠኞቹ በየለቱ እንዲያስፈጽሙ ጠይቀዋል። ቢሯቸውም ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ ስራው እንደሆነ ጨምረዋል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ቻርተር የመጀመሪያ አንቀጽ በጋዜጠንነት ሙያ ወሳኝና አስፈላጊ መርሆች ተደርገው የሚቀመጡ መሰረቶችን ያካተተ ነው። የአሜሪካ ድምጽ የታመነና የማያወላውል መረጃን ይሰጣል፤ ዜናው እውነታን መሰረት አድርጎ የተሟላና ሚዛናዊ ሊሆን ይገባል ይላል።

የቪኦኤ የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ ጉዌን ዲላርድ ለመገናኛ ብዙሃን ስራ አመች ባልሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አካባቢዎች የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስራ አያወላውልም ይላሉ

ሰሞኑን በተለያዩ ድረ-ገጾች፣ ብሎጎችና የሬድዮ ጣቢያዎች የቪኦኤን የውስጥ አሰራር አስመልክቶ የተነሱ አስተያየቶችንና ዘገባዎችን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾችን በዝርዝር እንመልከት።

የአፍሪካ ቀንድ ስራ አስኪያጅ ዲቪድ አርኖልድ ፤ ቪኦኤን የሚያስተዳድረው Broadcasting Board of Governors የኢትዮጵያን ጉብኝት ተከትሎ፤ ለአማርኛው ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት ሁኔታው እስኪጣራ በእረፍት እንዲቆዩ ተደርገው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ እንግሊዝኛው ክፍል ተዛውረዋል። ይኽ ለምን እንደሆነ ሬዲሽ ሲናገሩ፤

“የዴቭድ አርሎንድ ጉዳይ ስለሚገኝበት ህኔታ መናገር አልፈልግም። ዴቪድ አርሎንድ በቪኦኤ ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጠው ነው። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ሰራተኛ መብቶች አሉት። በቀረበው ዜና ላይ ተፈጥሯል በተባለው የመረጃ መዛባትም ሆነ በተላለፈው ቃለ ምልልስ ውስጥ እርሱ ስለነበረው ሚና እየፈተሽን ነው። ፍተሻው እንዳለቀ ዴቪድ አርሎንድ ምን እንደሚሰራ እንወስናለን።”

በአማርኛው ዝግጅት በድረ-ገጹ አስፍሮት የነበረው ዘገባ መነሳቱ፤ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ይጻረራል በሚል በርካታ ዘገባዎችና አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ታማኝ በየነም ይሄንን ያስተጋባል።

“ቦርድ ኦቭ ገቨርናንስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ የወጣ ዜና ነበረ። ዜናው ከወጣ በኋላ እንዲነሳ ተደርጓል። ይኽ ሴንሰር ነው። ሕዝብ ሊሰማው የሚገባው ነገር መነሳቱ ተገቢ አይደለም።”

ሌላኛው የውይይት ርእስ፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት የተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባን ጋዜጠኛ ልኮ ዘግቦ አየር ላይ እንዳይውል ተከልክሏል የሚል ነው። የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ ጉዌን ዲላርድ ይሄ መረጃ የተሳሳተ ነው ይላሉ። የአሜሪካ ድምጽ መጀመሪያውኑም ጋዜጠኛ አላከም ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ለተቃዋሚዎች ያደላል፤ በሃገር ውስጥ መንግስት የሚሰራቸውን የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የአገር ገጽታዎችና የአስተዳድር እመርታዎች ዋጋ ይነሳል ሲል ይከሳል።

በዚህ ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት አስተያየት እንዲሰጥ እድሉን ሰጥተን መልስ አስልሰጡንም። በዋሽንግተን የምገኘውን ኢምባሲና የመንግስቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ያደረግንው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም።

የኢትዮጵያ መንግስት 42 ገጽ ያለው የክስ መዝገብ ለአሜሪካ ኢምባሲና ለቪኦኤ አስገብቷል። ባለፉት ጥቂት ወራት የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስርጭቶች ላይ መንግስቱ ያልወደዳቸውንና ሚዛናዊ ያልሆኑ ያላቸውን ዘገባዎች አትቷል።

በዚህ ላይ የቪኦኤ አስተዳደር ጉዳዩን በገለልተኛ አካላት እያስጠና መሆኑን ስቲብ ሬዲሽ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በደፈናው ቪኦኤ የተሟሉ ዘገባዎችን አያቀርብም ከማለት ይልቅ ዝርዝር ክስ ማቅረቡ፤ የተሻለ አሰራር መሆኑ የጠቆሙት ሬዲሽ፤ ለዚህም ቪኦኤ በገለልተኛ አካላት የተጠና ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG