በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአዲስ አበባ አወሊያ መስጊድ ፖሊስና ሙስሊሞች ተጋጩ


ፖሊስ የአስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ በመስጊዱ የተሰባሰቡትን ሰዎች ሲበትን መመልከታቸውን ምስክሮች ገልጸዋል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም መግለጫ ሰጥቷል

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን በማስተናገድ ላይ በምትገኘው አዲስ አበባ ትናንት ማምሻውን ፖሊስና በአወሊያ መስጊድ አቅራቢያ የተሰባሰቡ ሰዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ከመቶ በላይ መታሰራቸውንና መቁሰላቸውን፤ የእስልምና ኮሚቴው ገለጸ።

የኮሚቴውን ቃል አቀባይ አህመዲን ጀበል ጠቅሶ የብሉምበርግ የዜና አውታር እንደዘገበውና፤ የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው የአይን ምስክሮችና አንዳንድ የኢንተርኔት ፎቶዎች እንደሚያሳዩት፤ ግጭቱ ጥይት፣ ቆመጥ፣ ድንጋይና አስለቃሽ ጋዝ የተተኮሰበት ነው። በዚህ ግጭት አንድ ሰው ሳይገደል እንዳልቀረ ኮሚቴው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚውኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚንስትር ድዔታ አቶ ሽመልስ ከማል ለብሉምበርግ የዜና አውታር፤ በግጭቱ 72 ሰዎች መታሰራቸውንና ስድስት የፖሊስ ባልደረባዎችን ጨምሮ 10 ሰላማዊ ሰዎች የቆሰሉበት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም በአወሊያ ት/ቤትና መስጊድ አቅራቢያ መንገድ በመዝጋት የፖለቲካ መፈክር ያሰሙ የነበሩትን ሰዎች ፖሊስ በአስለቃሽ ጋዝ መበተኑን ተናግረዋል። ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጥይት አለመተኮሱን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

በአወሊያ መስጊድ የተሰባሰቡ ሰዎችን ወክለው ለብሉምበርግ የዜና አውታር መግለጫ የሰጡት አህመዲን ጀበል ፖሊስ በአወሊያ መስጊድ ተሰባሰበው በሰላይ የተቀመጡ ሙስሊሞች ላይ አጥር ጥሶ በመግባት፣ ጥቃት ማድረሱን ተናግረዋል።

“በሩን ሰብረው ገብተው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ተኩስ ከፈቱ” ብለዋል አቶ አህመዲን።

በኢትዮጵያ መንግስትና በእልምና ምክር ቤቱና ደጋፊዎቹ መካከል ግጭቱ የተባባሰው፤ መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ ነው በሚል በምክር ቤቱ በተነሳ ቅሬታ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የሃይማኖት ጉዳዮችን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ይተው፤ መሪዎቻችንን እራሳችን እንምረጥ ይላል፤ ምክር ቤቱ።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ምክር ቤቱ በውስጡ የፖለቲካ ተልእኮ ያላቸውና ኢትዮጵያን በእስላማዊ ህግ የምትመራ አገር የማድረግ ጽንፍ የረገጠ አክራሪነት ያለባቸው አካላትን አካቷል ሲል ወንጅሏል።

ይሄ አስተያየት የተሰማው በሚያዝያ ወር በአርሲ አሳሳ ከተማ ውስጥ አንድ የእስልምና አባት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይመራሉ በሚል በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተቀሰቀሰ ግጭት 4 ሰዎች ከተገደሉና በርካቶች ከታሰሩ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል በአዲስ አበባ ትናንት ማምሻውን የተቀሰቀሰው ግጭት መብረዱንና ሁኔታው በቁጥጥር ስር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መሪዎችን በምታስተናግድበት ወቅት አንዳንድ ሃይሎች ብጥብጥ ለመፍጠር እየጣሩ ናቸው በለዋል አቶ ሽመልስ ከማል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG